የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች የጠቅላዩ የጀግንነት ተጋድሎ ለተጨማሪ ድጋፍና ደጀንነት እንዳነሳሳቸው ገለጹ

75

መተማ (ኢዜአ) ህዳር 22/2014 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ሌሎች አመራሮች በግንባር እየፈጸሙት ያለው የጀግንነት ተጋድሎ ለተጨማሪ ድጋፍና የደጀንነት ተግባር እንዳነሳሳቸው የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ይርሳው ስጦታው ለኢዜአ እንዳሉት አሸባሪው ቡድን የከፈተው ጦርነት የኢትዮጵያን ህዝብ ወደ ቀደመ አንድነቱ እንዲመለስ አድርጓል።

ሁለት ልጆቻቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለው የሽብር ቡድኑ በንጹሀን ላይ የሚፈጽመውን ግፍና ወረራ ለመመከት በጀግንነት እየተፋለሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።

"ኢትዮጵያዊያን የአሸባሪ ቡድኑን የጥፋት ተግባር በመመከት እያስመዘገቡት ባለው አዲስ ታሪክ ልጆቼ ተሳታፊ በመሆናቸው ኩራት ይሰማኛል" ሲሉም ተናግረዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩና በየደረጃው ያሉ አመራሮች በአውደ ግንባር መዝመት በሌሎች ላይ መነሳሳት ፈጥሯል" ያሉት አቶ ይርሳው፣ እሳቸውም ለሠራዊቱ ተጨማሪ ድጋፍና ደጀን ለመሆን መነሳታቸውን ተናግረዋል።  

በአሁኑ ወቅትም በስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት ግንባር ተሰልፈው አሸባሪህን ህወሓት እየተፋለመ ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል ሀብት በማሰባሰብ የደጀንነት ሥራ እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት።

"በተለይ አሁን ጠቅላይ ሚንስትሩ በግንባር የሕልውና ጦርነቱን መምራት ከጀመሩ በኋላ እየመጣ ያለው ለውጥ እኔን ጨምሮ ብዙዎችን ድጋፋችንን እንድናጠናክር አድርጎናል" ብለዋል።

"ከዚህ በፊት 4ሺህ ብር እና ሌሎች ቁሶችን ለፀጥታ ኃይሉ ድጋፍ አድርጊያለሁ" ያሉት አቶ ይርሳው፣ በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በከተማው በሆቴል ሥራ የተሰማሩት ሌላኛው ነዋሪ ወይዘሮ አትጠገብ ከፋለ በበኩላቸው "ሰርቶ መለወጥና ሀብት ማፍራት የሚቻለው ሀገር ሰላም ሲሆን ነው" ብለዋል።  

ኢትዮጵያ ሰላም ካልሆነች አሁን ያላቸው ሀብትና ንብረት ስለማይኖር ኢትዮጵያን ከአፍራሽ ቡድኖች ለመጠበቅ ካላቸው ቀንሰው ለፀጥታ አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ በፊትም 5ሺህ ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመትን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሠራዊቱ ላይ የታየው መነቃቃት ብርታት እንደሆናቸው ጠቁመዋል

"ጦርነቱ በድል እስኪጠናቀቅ ደረስ በምችለው ሁሉ ድጋፌን ለመቀጠል ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።

"በህልውና ዘመቻው የቻለ በግንባር ሲሰለፍ መዝመት የማይችለው ከእለት ጉርሱና ከዓመት ልብሱ ቀንሶ በስንቅ ዝግጅት ዘመቻውን መቀላቀል ይኖርበታል" ብለዋል።

"እኔም በስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት ግንባር ተሰልፌ ለሠራዊቱ ደጀንነቴን እያሳየሁ ነው" ያሉት ነዋሪዋ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች አመራሮች የግንባር ተጋድሎና እየተሰማ ያለው ውጤት ድጋፋችንን ለማጠናከር አነሳስቶናል" ብለዋል።

የአባት አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አርበኛ በቀለ ጀምበር እንዳሉት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባር አመራርነት እየመጣ ያለው ለውጥ የኢትዮጵያ ቀጣይ ተስፋ በልጆቿ መስዋዕትነት የለመለመ ስለመሆኑ ያሳያል።

"ኢትዮጵያ አሁን የገባችበትን የህልውና ዘመቻ በድል ከተጠወጣች ዳግም አድዋን በማስመዝገብ በቀጠናው ብሎም በመላ አፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆና መቀጠል የሚያስችላት አጋጣሚ ይፈጠራል" ብለዋል

ለህልውና ዘመቻው ማህብራቸው ከ40 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ፍየሎችንና የምግብ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው፤ አሁንም ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  ጠቁመዋል።

በዘመቻው ሁሉም የእኔ ተሳትፎ ምን ሊሆን ይገባል ብሎ በመጠየቅ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አርበኛው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም