አሸባሪው ህወሃት ልዩነትን ለማስፋት ቢደክምም የክልሉ ህዝቦች አብሮነታቸውን አጠናክረው ቆይተዋል

197

ሶዶ፤ ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት የመቻቻል እሴቶችን ለመሸርሸር ልዩነት እንዲሰፋ ቢደክምም የክልሉ ህዝቦች አብሮነታቸውን አጠናክረው መቆየታቸውን የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ገለጹ።

“ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊነት” በሚል መሪ ሀሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከበረ ባለው የመቻቻል ቀን  በክልል ደረጃ የ”በቃ” ንቅናቄ እንደሚጀመር ይጠበቃል።  

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዳሉት፤ በክልሉ ያሉ የመቻቻል እሴቶችን በማጠናከር ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማምጣት መጠቀም ይገባል።

እነዚህ በርካታ የተለያየ ባህል፣ ዕምነትና ቋንቋ ያሏቸው  የክልሉ ህዝቦች በመቻቻል እሴቶቻቸው  በአንድነትና በሰላም አብረው እንዲኖሩ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት እነዚህን እሴቶች ለመሸርሸር ልዩነትን እንዲሰፋ ቢደክምም የክልሉ ህዝቦች  አብሮነታቸውን አጠናክረው  መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ሀገራችን የተደቀነባትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ መላው ህዝብ ልዩነቱን በማቻቻል አንድነቱን አጠናክሮ ለመቀጥል እያደረገ ባለው ርብርብ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም አቶ ለማ ጠቁመዋል።

በየወቅቱ የሚነሱ  ጥያቄዎችን በመተው አሁን ላይ ለሀገር ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ኢትዮጵያን ለማዳን መቻቻል ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ አንድነታችንን አጠናክረን የጽንፈኞችን ዓላማ በማክሸፍ የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ መረባረብ የሚጠይቅበት ነው ያሉት።

የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤትና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያዘጋጁት  የመቻቻል ቀን በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉና የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።