በአማራ ክልል ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ይጠበቃል

184

ባህር ዳር ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በ2013/14 የመኸር እርሻ ሰሊጥ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤልያስ በላይ እንደገለጹት በክልሉ በ2013/14 የመኸር ምርት ዘመን ከ378 ሺህ 440 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማው የሰሊጥ  ሰብል በወቅቱ ተሰብስቧል።  

ባለሙያው እንዳሉት በክልሉ አዊ፣ ማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች  ከለማው መሬት ከ2 ሚሊዮን 270ሺህ  ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ይጠበቃል።

በክልሉ በምርት ዘመኑ ገበያ ተኮር ለሆኑ ሰብሎች ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በዘንድሮው የመኸር እርሻ በሰሊጥ የለማው መሬት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ154 ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

እንዲሁም  በምርት ዘመኑ የሚጠበቀውም የሰሊጥ ምርት ደግሞ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ732 ሺህ ኩንታል ያህል ብልጫ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

ምርቱ ከብክነት በፀዳ መልኩ እንዲሰበሰብ መደረጉን ገልጸው፤ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ሰሊጥ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሀገሪቱ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል።