ደቡብ ሱዳን ሁሉን አቀፍ የሥምምነት ማዕቀፍ ለማጽደቅ መወሰኗ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማነት ያሳያል

114

ህዳር 23/2014/ኢዜአ/ ደቡብ ሱዳን የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ አካል የሆነውን ሁሉን አቀፍ የሥምምነት ማዕቀፍ ለማጽደቅ መወሰኗ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማነትን የሚያሳይ መሆኑ ተጠቆመ።


እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1999 በአስር የናይል ወንዝ ተፋሰስ አገራት የተቋቋመው የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የናይል ውኃን በትብብር ለማልማትና ለመጠቀም ትልቅ መሰረት ጥሏል።      

ኢኒሼቲቩ ውኃን በፍትኃዊነትና በእኩልነት መጠቀም የሚለውን መርህ ሕጋዊ መሠረት ለማስያዝ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 ሁሉን አቀፍ የሥምምነት ማዕቀፍም አውጥቷል።

በሥምምነት ማዕቀፉ መሠረት ሕጋዊና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚመራ የናይል ኮሚሽን ይቋቋማል፤ ይህንንም ማዕቀፍ ወደ ሥራ ለማስገባት ስድስት አገራት ማዕቀፉን ማጽደቅ ይጠበቅባቸዋል።

እስካሁንም ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ዩጋንዳ በማጽደቅ የአገራቸው የሕግ አካል ያደረጉ ሲሆን ደቡብ ሱዳንም በሕግ አውጪ አካሏ ለማጽደቅ መዘጋጀቷን ከቀናት በፊት ገልጻለች።

ይህም ኢትዮጵያ ወንዙን በጋራ የመጠቀም መርህን እውን ለማድረግ እያካሄደች ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማነት እንደሚያመላክት ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ የሚናገሩት።

የሥምምነት ማዕቀፉን ወደ ሥራ ለማስገባት ከደቡብ ሱዳን ውጪ አንድ ተጨማሪ የተፋሰሱ አገር ማጽደቅ እንዳለበት ጠቁመው ይህንንም እውን ለማድረግ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶቹ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን አባይ የሁሉም የተፋሰሱ አገራት የጋራ ኃብት መሆኑን በተለያዩ ቋንቋዎች ማስገንዘብ እንደሚገባቸው ገልጸው በተለይም ውኃውን የሚጋሩ ጎረቤት አገራት ሕዝቦችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሥምምነት ማዕቀፉን ስድስት አገራት አጽድቀውት ወደ ሥራ ከገባ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የምታራምደው የፍትሀዊ ተጠቃሚነት መርህ እውን እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

ግብጽና ሱዳን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚጻረረውን በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን የ1959ኙን የተናጠል ሥምምነት ያማከለ አቋም በማራመዳቸው የሥምምነት ማዕቀፉን ሊያጸድቁት አልቻሉም።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም