ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ከወቅቱ የስደተኞች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ድጋፍ እያቀረቡ አይደለም

145

ህዳር 23/2014( ኢዜአ) ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ከወቅቱ የስደተኞች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ድጋፍ እያቀረቡ እንዳልሆኑ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ገለጸ።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አገልግሎት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩ ኤን ኤች ሲ አር) እና አጋር አካላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ የስደተኞች ጉዳይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ጉዳይና ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አሁን ላይ በዓለም ላይ 90 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችና ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛዎቹ ስደተኞችና ተፈናቃዮች የሚገኙት በተለይም በአፍሪካ አገራት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያም ከተለያዩ ጎረቤት አገራት የመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች መኖራቸውን ገልጸው  ከለላ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፤ እየተደረጉም ይገኛሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ካሉት የስደተኞች ቁጥር አንጻር ግን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተመጠጣኝ የሆነ ድጋፍ እየቀረበ እንዳልሆነ አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።

ለስደተኞች አስፈላጊ ግብአቶችን፣ የስራ እድል መፍጠርን እና ሌሎችንም አገልግሎቶችን ማቅረብ ከተቻለ ለስደተኞችም ሆነ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ያስችላል ይላሉ።

በመሆኑም አለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶችና ሌሎች እርዳታ ሰጪ አካላት ለስደተኞች የሚውሉ እርዳታዎችን በአግባቡ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩ ኤን ኤች ሲ አር) ተወካይ ማማዱ ዲያን በበኩላቸው፤ በየትኛውም አካባቢ ያሉ ስደተኞች ተገቢ የሆነ ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። 

ለስደተኞች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ነጻ በሆነ መልኩ በገለልተኝነት ድጋፍ ማድረግ የሚገባ መሆኑን በመገንዘብ ድጋፍ መስጠት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የመንግስታቱ ድርጅትም ድጋፍና እገዛ ለሚያሻቸው ሰዎች ሁሉ ሰብአዊነትን ብቻ መሰረት ባደረገ መልኩ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በመቀበል ከዩጋንዳ ቀጥላ በአፍሪካ ሁለተኛ ስትሆን የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሌ፣ የኤርትራና ሱዳን እንዲሁም የሌሎች አገራት ስደተኞች ይገኛሉ።