በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ የተጋለጡ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው

171

ህዳር 23/2014( ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ የተጋለጡ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ፡

አሸባሪ ቡድኑ ከሰሞኑን በአፋር ክልል ጭፍራ ግንባር በወገን ጦር ሽንፈት ገጥሞት ከመፈርጠጡ በፊት ንጹሃንን ጨፍጭፏል፤ ዘረፋ ፈጽሟል፤ የእምነት ተቋማትን ጨምሮ ሃብት አውድሟል፡፡

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በጭፍራ ከተማ በመገኘት አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰውን ውድመትና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን  ጎብኝቷል፡፡

አሸባሪው ቡድኑ በከተማዋ ያደረሰው ውድመትና ሰብዓዊ ቀውስ እጅግ አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ የተጋለጡ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ደግሞ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

አሸባሪው ህወሃት በወገን ጦር የተቀናጀ ማጥቃት ሽንፈት እየተከናነበ በመሸሽ ላይ ሲሆን፤ በቅርቡም አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው የነበሩ በርካታ ቦታዎች ነጻ መውጣታቸው ይታወቃል፡፡

የወገን ጦርን መቋቋም አቅቷቸው በመሸሽ ላይ የሚገኙት የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች ንብረት እንዳይዘርፉና እንዳያወድሙ ኀብረተሰቡ ተደራጅቶ አከባቢውን እንዲጠበቅ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡