የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዚህ ዓመት የቢዝነስ ተጓዦች የአፍሪካ ምርጥ በመሆን አሸነፈ

63

ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2021 የቢዝነስ ተጓዦች ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማት አሸናፊ ሆነ።

በአፍሪካ ግዙፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆነው ''ቢዝነስ ትራቭለርስ ''መጽሄት የሚያዘጋጀውን ሽልማት ነው በምርጥነት ያሸነፈው።

የዚህ ዓመት ሽልማት የ24 ወራት የደንበኞች ምልከታ የሸፈነ በመሆኑ ከቀደሙት ሽልማቶች ይበልጥ ሰፊ ልምዶች የተንጸባረቁበት መሆኑን አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህ ዓመት በንግድ ተጓዦች የተሰጡ ድምጾች የአየር መንገዶችን የተግባቦትና የኮሮና ወረርሽኝ የጥንቃቄ እርምጃዎች ውጤታማነት ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም በተሳፋሪዎች አያያዝ እና በሚጣልበት እምነት እንዲሁም የቲኬት ለውጦችን በማድረግ ረገድ የሚኖረው ተባባሪነት የወረርሽኙን ጊዜን ታሳቢ ያደረጉ ጥያቄዎች በሽልማት መስፈርትነት የተካተቱበት ነበር።

ጥያቄዎቹ ተጓዦች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ በፊት እና በተለያዩ ጊዜያት ያካበቱትን ሰፊ ልምድ እንዲያንፀባርቁ ያስቻለ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ሽልማቱን አስመልክተው እንዳሉት ይህ የላቀ ሽልማት የአየር መንገዱ የደንበኞች እርካታ ነጸብራቅ ነው።

ሽልማቱ አየር መንገዱ በሁሉም ቦታ የላቀ የደንበኞች አገልግሎት ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት ስኬት የሚያሳይ በመሆኑ የሚያስደስት ነው ብለዋል።

አቶ ተወልደ አክለውም “ሽልማቱ በየእለቱ የደንበኞቻችንን እርካታ፣ ደህንነት እና ምቾትን ለማረጋገጥ ከ17 ሺህ የሚበልጡ የስራ ባልደረቦቻችን ያደረጉትን የላቀ ጥረት እና እንክብካቤ የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዓለም የጤና ስጋት ሆኖ በተከሰተበት ወቅት ጭምር ለደንበኞች የሚሰጠውን የበረራ አገልግሎት አለማቆሙ የሚታወቅ ነው።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም