የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ እየወሰደ ያለው እርምጃ አበረታች ነው - ክሪስ ስሚዝ

81
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ እየወሰደ ያለው እርምጃ አበረታች ነው ሲሉ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አባል ክሪስ ስሚዝ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የአፍሪካ የዓለም አቀፍ ጤና፣ ሰብዓዊ መብቶችና ተቋማት ንዑስ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የሆኑትን ክሪስ ስሚዝን እና የንዑስ ኮሚቴው አባል ሚስ ካረን ባስን ዛሬ አነጋግረዋል። የንዑስ ኮሚቴው ሊቀ-መንበር ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጵያ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ መንግስት እያከናወነ ያለው ተግባር ግልፅ የሆኑ ለውጦች የሚታዩበት ነው ሲሉ ተናገረዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የገለፁት ክሪስ ስሚዝ እርምጃዎቹ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችልም ከወዲሁ ምልክቶች እየታዩ ነው ብለዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ያደረጉት ንግግር በጣም አስገራሚና ለለውጥ ያላቸውን ፍላጎት ያሳየ ነበር" ሲሉም ሁኔታውን አስታውሰዋል። "በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠላት ሳይሆኑ ተፎካካሪ መሆናቸውን፣ ስለ እናታቸውና የትዳር ጓደኛቸው የተናገሩት ነገር፤ ስለ ኢትዮጵያ ቀጣይ ዕድገትና ተስፋ እንዲሁም ስለ ቤተሰብ ተቆርቋሪነታቸው የሚያሳይ ነው" ብለዋል። ክሪስ ስሚዝ ከዶክተር ወርቅነህ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል በተለያየ መስክ ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መነጋገራቸውንም ገልፀዋል። በተለይም የዘመኑ ባርነት የሆነውን ህገ - ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዶክተር ወርቅነሀ ጋር መምከራቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ቆይታቸው ያገኙትን መረጃ ጨምሮ አጠቃላይ ጉብኝታቸውን በተመለከተ የአሜሪካ ኮንግረስ ቋሚ ኮሚቴዎች በሚያደርጉት ውይይት ላይ እንደሚቀርብና ባለሙያዎችም አስተያየት እንደሚሰጡበት አመልክተዋል። የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የአፍሪካ የዓለም አቀፍ ጤና፣ ሰብአዊ መብቶችና ተቋማት ንዑስ ኮሚቴ አባል ሚስ ካረን ባስ በበኩላቸው በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎች በጣም አበረታች የሚባሉ መሆናቸውን ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረት መልካም የሚባል ነው ሲሉም ሚስ ካረን ተናግረዋል። የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ሆነው የተወከሉባት የሎስ አንጀለስ ከተማ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩባት ከመሆኑ አንጻር "ትንሿ ኢትዮጵያ" እንደምትባል ገልጸዋል። በከተማዋ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ስላለው ለውጥ እንደሚነግሩና አንዳንዶቹ ካሳቡበት ጊዜ ቀደም ብለው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚያበረታቱም ቃል ገብተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት መሆኑን በመጠቆም አሜሪካ ለኢትዮጵያ ዕድገት ለምታደርገው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በልማት፣ በዴሞክራሲ፣ በመልካም አስተዳደር እና በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር መስራቷን እንደምትቀጠልና  ኮንግረሱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የአሜሪካ ኮንግረስ በድረ-ገጹ ባሰፈረው መረጃ ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም በፊት H.Res.128 በሚል ባጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ሰብአዊ መብት እንዲሁም በመሰብሰብ መብትና የሚዲያ ነጻነት፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቷ ፖለቲካ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ እየተወሰደ ያለው እርምጃና አዋጆችን ለማሻሻል ባቀረባቸው ሀሳቦች ላይ መንግስት ተጫባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልጿል። ከሁለት ሺህ በላይ እስረኞች መፈታታቸውም እንደ ዋንኛ ማሳያ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም