አሸባሪው ህወሓት የእምነት ተቋማትንና ቅዱሳን መጽሃፍትን በማቃጠል ለሃይማኖቶች ያለውን ጥላቻ በተግባር አሳይቷል

95

አዲስ አበባ ፣ህዳር 23/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን የእምነት ተቋማትንና ቅዱሳን መጽሃፍትን በማቃጠል ለሃይማኖቶች እያሳየ ያለውን ጥላቻና ንቀት የእስልምና ሃይማኖት አባቶች አወገዙ፡፡ 

አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዘባቸው አካባቢዎች የእምነት ተቋማትን አውድሟል፤ አንዳንዶቹን ደግሞ የጦርነት ምሽግ በማድረግ ለሃይማኖትም ሆነ ለሰው ልጆች ክብር የሌለው መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ከሰሞኑን በአፋር ክልል ጭፍራና ካሳ ጊታ ግንባሮች በወገን ጦር ሽንፈት ገጥሞት ከመፈርጠጡ በፊት ቅዱስ ቁርዓንን እና መስጂዶችን አቃጥሏል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና ሃይማኖት አባቶች እንደሚሉት፤ አሸባሪ ቡድኑ ህዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበትን፣ፈጣሪውን የሚያመልክበትን ቅዱስ ስፍራ ላይ አረመኔያዊ ተግባር በመፈጸም ሃይማኖቱን የማርከስ ስራ ሰርቷል።

በዚህም ለእስልምና እምነት ያለውን ጥላቻ በተግባር አሳይቷል ነው ያለት፡፡

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እና የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሐመድ ሲራጅ፤ የሽብር ቡድኑ የፈጸመው ተግባር በእስልምና አስተምሮ በእጅጉ የተወገዘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚቃወምም ነው የገለጹት፡፡

በእስልምና አስተምህሮ ላይ ምርምር እያደረጉ የሚገኙት ሼክ አህመድ አወል በእስልምና ሃይማኖት ቅዱስ ቁርዓንና መስጂድ ታላቅ ክብር የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ቅዱስ ቁርዓንና መስጂድን በማቃጠል በዓለም ላይ ላሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያለውን ጥላቻ በግልጽ ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡

አሸባሪው ቡድን  ቅድስ ቁርዓንና መስጂዶችን ከማቃጠል ባሻገር በእምነት ቦታዎች ላይ ወንጀል መፈጸሙንም ነው ያነሱት፡፡

ሼክ አህመድ አወል ጨምረውም በእስልምና ውስጥ ቅዱስ ቁርዓን ትልቅ ቦታ አለው፣ሙስሊሞች የህይወት ጉዛአቸውን በቁርዓን መቅረጽ አለባቸው በቁርዓን መመሪያ መታነጽ እንዳለባቸው በጣም ያሳስባል።

"ስለዚህም ቅዱስ ቁርዓን በእስልምና ሃይማኖት ውሰጥ በጣም ትልቅ ቦታ ያለው መከበር ያለበት ሌላ ቀርቶ እንኳን በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ምንም አይነት ፊደል ፣ሃሳብም መቀየር ፣መለወጥ ምንም የማይቻል ብቸኛው መመሪያችን ቅዱስ ቁርዓን ነው" ብለዋል።

በዚህም "ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ" እንዲሉ ለእምነትና ለእምነቱ ተከታዮች ያለውን ንቀትና ጥላቻ ማሳየቱንም ነው" ያብራሩት፡፡

ሼህ መሐመድ ሲራጅ በበኩላቸው መስጂድ ተቃጥሏል፣ ቁርዓን ተቃጥሏል በዚህ ሳያበቃ የእምነቱን ቦታ እራሱ ምሽግ አድርጎ ተጠቅሞበታል ብለዋል፡፡

ለእምነቱ ያለው የወረደ አመለካከት፣ለእምነቱ ባለቤቶች ያለው ንቀትና የቆሸሸ አመለካከት የሚያሳይ ነው ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት ሰሞኑን በአፋር ክልል ካቃጠለው ቅዱስ ቁርዓን ላይ "የጀሃነብ እሳት መቀጣጠያ ናቸው" የሚለው ቃል እንደተረፈ ገልጸው፤ ይህም የሽብር ቡድኑ አባላት ከፈጣሪ ቁጣ እንደማይተርፉ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በየትኛውም የእምነት ተቋማት ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት እንደሚያወግዙ የገለጹት የሃይማኖት አባቶች፤ በመሆኑም የሽብር ቡድኑን በተባበረ ክንድ መመከት አለብን ብለዋል፡፡

በቡድኑ ወረራ ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም