በዞኑ ከ14ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በቆላ ስንዴ ዘር ተሸፍኗል

79

አዳማ፤ ህዳር 23/2014/ኢዜአ/ በምስራቅ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ከ14ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በቆላ ስንዴ ዘር መሸፈኑን የዞኑ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 10 ወረዳዎች ከ35ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የቆላ ስንዴ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ14ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

የቆላ ስንዴ ልማቱ በተሻሻሉ የግብርና መሳሪያዎች በመታገዝ በኩታ ገጠም ማሳ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል ።

አርሶ አደሩ በዘርፉ ልማት ለመሳተፍ እያሳየ ያለው ፍላጎትና ተነሳሽነት እጅጉን እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት አቶ መስፍን በሸንኮራ አገዳ ያልለሙና እስከ አሁን አገልግሎት ላይ ያልዋሉ መሬቶች ጭምር በቆላ ስንዴ እንዲለሙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የሰብሉን ምርታማነት ለማሳደግ የምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ፀረ አረም ኬሚካል በተሻለ አግባብ እየቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዘንድሮ የቆላ ስንዴ ልማት እስከ 100 የፈረስ ጉልበት ያላችው 320 አዳዲስ የውሃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች መቅረባቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት 473  ጄኔሬተሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ  እጥረት፣የመስኖ ቦዮችን ጠግኖ ወደ ስራ ማስገባት በዘርፉ እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቁመው ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ከክልሉ መንግስትና ምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅቶችና ዩኒዬኖች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።

አቶ መስፍን አክለው የቆላ ስንዴ የመስኖ ልማት በዞኑ በሚገኙ 10 ወረዳዎች ላይ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው  በመጀመሪያ ዙር  ልማቱ ከ50ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በምስራቅ ሸዋ ዞን የአዳማ ወረዳ በወንጂ ኩሩፍቱ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በቆላ ስንዴ የመስኖ ልማት ከተሰማሩ መካከል አርሶ አደር ተሾመ አበጋዝ እንደገለጹት በሸንኮራ አብቃይ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ተደራጅተው ሸንኮራ በማምረት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ሲመሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

"የአገዳ ልማት ኪሳራ የሚበዛበት ከመሆኑም ባለፈ ኑሮን መዶጎምና ልጆችን ማስተማር አቅቶን ነበር" ያሉት አርሶ አደሩ ለ18 ወራት ሸንኮራ አምርተው  የሚያገኙት ገቢ 5ሺህ ብር ብቻ እንደነበር ጠቅሰዋል።

 አሁን ላይ ፊታቸውን ወደ ቆላ ስንዴ በማዞር 180 አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው በ335 ሄክታር በኩታ ገጠም መሬት ላይ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

 "ከዚህ ቀደም መሬታችን ያለጥቅም ይቀመጥ ነበር፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስት ባቀረበልን ድጋፍ መሰረት ስንዴ እያለማን ነው" ያሉት ደግሞ አርሶ አድር አለማየሁ በልሁ ናቸው።

"መሬታችን የሸንኮራ አገዳ ማሳ ሆኖም ምንም ውጤት ሳናገኝበት ከ40 ዓመታት በላይ ጦሙን አድሮ ነበር" ያሉት አርሶ አደር አለማየሁ "መንግስት ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የውሃ መሳቢያ ሞተርና የእርሻ ትራክተር አቅርቦልን ወደ ልማቱ ገብተናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም