የግሉን ሴክተር በማሳተፍ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ የሚታየውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ይሰራል

87

ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የግሉን ሴክተር በማሳተፍ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ የሚታየውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚሰራ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ገለፀ።

በቀጣይ ዘርፉን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ሕጎች እንዲፀድቁ እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አከናውኗል።

መድረኩ በዋናነት በትራንስፖርትና ሎጅስቲክ መሠረተ ልማት አግልግሎት መሟላት ያለባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ለመመልከት መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ዘርፉ ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የፋይናንስና የማስፈጸም አቅም ውስንነት ዋነኛቹ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የግሉ ሴክተርን በዘርፉ ንቁ ተሳታፊ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ የትኞቹ ተግባራት ለግሉ ሴክተር መሰጠት እንዳለባቸው የመለየት ስራ እንደተከናወነም ተናግረዋል፡፡

የማስፈፀም አቅሙን ለማሳደግ ክልሎችን የሚያሳትፍ የአጭርና የረዥም ግዜ ስልጠና ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ዘርፉን ለማቀላጠፍ የሚረዱ ማስፈፀሚያ ሕጎችን ለማፀደቅ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።  

ከሚፀድቁት ሕጎች መካከል የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ፣ የመንገድ ደህንነት ተቋም ማቋቋሚያ ደንብና የፐብሊክ ትራንስፖርት ማሻሻያ ደንብ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የተሽከርካሪ መኪናዎች ክብደት ልክ መወሰኛ ረቂቅ ደንብ፣ የባለሞተር ተሸከርካሪዎች ፍጠነት ወሰን ማሻሻያ ደንብና የቀጣይ 30 ዓመት የትራንስፖርት መሪ ዕቅድ ይፀድቃል ነው ያሉት።

የተቀናጀና ደህንነቱ የተጠበቀ የሎጅስቲክና ትራንስፖርት አገልግሎት ለመፍጠርና ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ላይ አተኩሮ መሥራትም የዘርፉ ዋንኛ ትኩረት መሆኑን ገልፀዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም