በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ የሚገኙ 8 ሺህ 567 የመገናኛ፣ የመረጃና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ባለፉት 12 ቀናት ተመዝግበዋል

63

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ባለፉት 12 ቀናት በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ የሚገኙ 8 ሺህ 567 የመገናኛ፣ የመረጃና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን መመዝገቡን አስታወቀ።

ከህዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም የመገናኛ መረጃና ቴክኖሎጂ መሣሪያ ባለቤት ንብረቱን ማስመዝገብ እንዳለበት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ማሳሰቡ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት የተለያዩ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች በእጃቸው የሚገኙ የመገናኛ፣ መረጃና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን እያስመዘገቡ መሆኑን አስታውቋል።

በኤጀንሲው የመረጃ መገናኛና ቴክኖሎጂ እቃዎች ቁጥጥርና ውል ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ ተመስገን አስማረ፤ በማሳሰቢያው መሰረት የሳተላይት ስልክ፣ ወታደራዊ መነፅር፣ ጂፒኤስ፣ ድሮን፣ ቪስትናዊጋን እና የመገናኛ ሬዲዮኖች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ  ባለፉት 12 ቀናት ከተመዘገቡት መካከል 820 ወታደራዊ መነፅሮች፣ 764 የሳትላይት ስልኮች፣ 3 ሺህ 493 ጂፒኤስ እንዲሁም 191 ድሮኖች ተጠቃሽ ናቸው።

የምዝገባው ሂደት የፊታችን ዓርብ ድረስ እንደሚቀጥል ገልጸው አስካሁን ያላስመዘገቡ በቀሪዎቹ ቀናት ማስመዝገብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በተጠየቀው መሰረት ካስመዘገቡ በኋላ ህጋዊ ሆነው ስራዎቻቸውን ማከናወን ይችላሉ ነው ያሉት።

በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ያላስመዘገቡ ግለሰቦችና ተቋማት ግን በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑና ንብረታቸውም እንደሚወረስ ገልጸዋል።

ለማስመዝገብ መረጃ ለሚፈልጉ ሁሉ በስልክ ቁጥር 0900-67-23-42፣  0904-04-96-25 ፣ 011-3851193 ወይም 0114701321  መጠይቅ ይችላሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም