የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩ ያለውን ያልተገባ ጫና ለመመከት የምሁራን ተሳትፎ መጠናከር አለበት

106

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንድ አንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ያለውን ጣልቃ ገብነትና ያልተገባ ጫና ለመመከት የምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ።

“የምእራባውያን ጫና እና የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት የምሁራን ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጀሶ፤ የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ያለውን ጣልቃ ገብነትና ያልተገባ ጫና ለመመከት የምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሁሉም የሙያ ዘርፍ የሚገኙ ምሁራን እውቀትና ክህሎታቸውን በመጠቀም የኢትዮጵያ አለኝታ ሆነው መገኘት አለባቸው ብለዋል።

በህልውና ዘመቻው ምሁራኑ በተለይም በመረጃና ኮሙንኬሽን ግንባር በንቃት በመሰለፍ የኢትዮጵያን እውነታ ለመላው ዓለም በማስረዳት ግንባር ቀደም ሃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።

የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ ያለቸው  ፍላጎት ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ምን ልትከተል ይገባታል? ጫናውንና ጣልቃ ገብነቱን እንደት መመከት ይቻላል የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የምሁራኑ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት የሚፈፅመውን እኩይ ድርጊት አሜሪካና አንዳንድ የምራቡ ዓለም አገራት አይተው እንዳላዩ እያለፉት ነው ይላሉ።

አገራቱ እንዳውም የአሸባሪው ሃይል ደጋፊ በመሆን በኢትዮጵያ መንገስት ላይ ግልጽ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ጠቅሰው ድርጊታቸውን ለመመከት በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

የኮተቤ ትምህርት ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና፤ ኢትዮጵያ የሁላችንም በመሆኗ በጋራ የመጠበቅ ሃላፊነቱን የጋራ ሃላፊነታችን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም