ማህበሩ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ 33 ዓይነ-ሥውራን የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

182

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የዓይነ ሥውራን ብሔራዊ ማህበር በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ 33 ዓይነ-ሥውራን የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ይልማ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በርካታ አካል ጉዳተኞች ለችግር ተጋልጠዋል።

በመሆኑም ማህበሩ ከአባላቱ የሰበሰበውን ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ከቀያቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ችግር ውስጥ ለሚገኙ አይነ ስውራን ድጋፍ ማድረጉን ተናግሯል፡፡

እርዳታው ከተደረገላቸው ውስጥ ከሰቆጣ ከተማ የመጣው ወጣት አበበ ነጋሽ፤”ማህበሩ ችግር ላይ መሆናቸውን ተገንዝቦ  የገንዘብ ድጋፍ በማድረጉ የላቀ ምስጋናን ላቀርብ እወዳለሁ” ነው የሚለው።

በጦርነት፣መሰል ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ይበልጥ ተጠቂ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች መሆናቸውን በመገንዘብ ሌሎች ድርጅቶችም ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጠይቋል፡፡

ሌላው ከደሴ ከተማ እንደመጣ የሚናገረው አቶ መሀመድ ሀቢብ ማሕበሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርቦ፤ ሌሎች መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ ረገድ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከዚህ በፊት ማህበሩና አባላቱ  በተመሳሳይ ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ማድረጋቸውም ተገልጿል።