"ሀያላን ነን ያሉ ቢረባረቡብንም ሃያል የሆነ ወኔ ኢትዮጵያውያን ውሰጥ እንዳለ እያስመሰከርን ነው"-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

77

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ሀያላን ነን ያሉ ቢረባረቡብንም ሃያል የሆነ ወኔ ኢትዮጵያውያን ውስጥ እንዳለ ለአለም እያስመሰከርን ነው" ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባዋ ይህን ያሉት በከተማዋ የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶችና ሌሎች ተቋማት ለመከላከያ ሰራዊት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በገንዘብ ያደረጉትን ድጋፍ ባስረከቡበት ወቅት ነው።

ድጋፉን ያደረጉት የአዲሰ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የሴቶች ማህበርና የብልጽግና ሴቶች ሊግ፣ የምገባ ኤጀንሲና በመንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የሚመግቡ እናቶች ናቸው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እኛ  ኢትዮጵያውያን ሰላም ወዳድ መሆናችን ባያጠያይቅም "በአገር ህልውና ሲመጡብን ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ኋላ የምንለው ነገር የለም" ብለዋል።

ብዙዎች ሃያላን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ቢረባረቡም በአገራቸው ድርድር የማያውቁት ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን ለአለም እያሳዩ መሆኑንም አክለዋል።

በከተማዋ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የሚመግቡ እናቶች ለሰራዊቱ ስንቅ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ83 በሬ በላይ በቋንጣ መልክ በማዘጋጀት እያከናወኑ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው እሰከመጨረሻው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የአዲሰ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃናየሺ ንጉስ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ሴቶች አገር በምትፈልገው ሁሉ ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውን አረግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግንባር በመገኘት የህልውና ዘመቻውን በመምራት በየጦር ግንባሩ እያስመዘገቡ ላለው አንጸባራቂ ድል ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሎጂ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው ኢትዮጵያውያን እያደረጉ ያለውን ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፉ "መሪያችን ዘምቶ እኛ አንቀርም፣ መሳሪያ ባናነግብ ሰራዊቱን እንመግባለን" በሚል የተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም