አስተዳደሩ በአሸባሪው ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ወደ ሥፍራው ላከ

91

ድሬዳዋ፤ ህዳር 22/2014(ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ፈጽሞት በነበረው ወረራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ወደ ሥፍራው መላኩን አስታወቀ።

ድጋፉ የተላከው አስተዳደሩ   ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ካሰባሰበው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ  ሃብት ውስጥ ነው።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊና  የአስቸኳይ ጊዜ  የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሱልጣን አልይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአፋር ክልል  ለተፈናቀሉ  ወገኖች በጥሬ ገንዘብ  5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም  5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የአልባሳትና የምግብ ቁሶች ትናንት ወደ ሥፍራው ተልኳል፡፡

ከድጋፉ ውስጥ ሩዝ፣ ቴምር፣ ፓስታ፣ ማኮሮኒ እና  አልባሳት ይገኙበታል፡፡

የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ለሀገር ህልውና መረጋገጥ በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ እየተሰበሰበ የሚገኘው ሃብትና የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ የኃይማኖት ተቋማትና የታክሲ አሽከርካሪዎች የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ ፣ደም በመለገስ እያደረጉ ከሚገኘው የደጀንነት ተግባራት ባለፈ ለሠራዊቱ በገንዘብና ቁሶች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ሀገርን ለማዳን በጀግንነት ህይወቱን እየሰዋ ለሚገኘው ለጀግናው ሠራዊትና በሽብርተኛው ቡድን የተፈናቀሉት ወገኖች ለመርዳት ለሶስተኛ ጊዜ በተደረገ የተቀናጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ 28 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና  12 ሚሊዮን 500ሺህ ብር  በዓይነት መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

ከተሰበሰበው ገንዘብና ቁሶች ውስጥ  አሸባሪው ህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ፈጽሞት በነበረው ወረራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ   ወገኖች መላክ መጀመሩን አረጋግጠዋል።

ቀሪው በድሬዳዋ አስተናጋጅነት ህዳር 29 ከሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በዓል በኋላ  ለሠራዊቱ፣ በአማራ ክልል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ እንዲሁም በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የቦረና ዞን ወገኖች  እናደርሳለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም