እየተደረገልን ባለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ልጆቻችንን ለማስተማርም ሆነ ለመንከባከብ አልተቸገርንም

171

ጎንደር ፤ ህዳር 22/2014(ኢዜአ) ባለሀብቶችን ጨምሮ በህብረተሰቡና ከተማ አስተዳደሩ እየተደረገልን ባለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ልጆቻችንን ለማስተማርም ሆነ ለመንከባከብ አልተቸገርንም ይላሉ በጎንደር ከተማ የሚኖሩ የዘማች ቤተሰቦች፡፡

በጎንደር የማራኪ ክፍለ ከተማ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ምግብ ነክ ቁሶችና የአልባሳት ድጋፍ ዛሬ ለዘማች ቤተሰቦች አበርክቷል፡፡

ድጋፉ ከተሰጣቸው የዘማች ቤተሰቦች መካከል ወይዘሮ ይታይሽ መልኬ፤  ባለቤቴ የህወሃት የሽብር ቡድንን በጀግንነት ሲፋለም ቢሰዋም  የጎንደር ከተማ ህዝብ ድጋፍና ክብካቤ አልተለየኝም ብለዋል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፡፡

እድሜው ለትምህርት የደረሰው ወንድ ልጃቸው ነጻ የትምህርት እድል ተሰጥቶት እየተማረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሚደረግልኝ ወርሃዊ ቀለብና የገንዘብ ድጋፍ ሁለት  ልጆቼን በመልካም ሁኔታ እያሳደኩ እገኛለሁ ያሉት ወይዘሮ ይታይሽ፤ ዛሬ ደግሞ የጤፍ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ጫማና የአልባሳት ድጋፍ በማግኘቴ ተደስቻለሁ ነው ያሉት።

ባላቤቴ የክተት ዘመቻው በመቀላቀል ወደ ግንባር ከዘመተ ጀምሮ ሶስት ልጆቼን በማሳደግ ላይ የምገኘው ህዝቡና ከተማ አስተዳደሩ በሚያደርጉልኝ ያልተቋረጠ ድጋፍ ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ወርቄ አዲስ ናቸው፡፡

ለትምህርት የደረሱ ሁለት ልጆቼ  የትምህርት ቁሳቁሶችና የደንብ ልብስ በህዝቡ ድጋፍ ተሸፍኖላቸው እየተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ የሺ ፈረደ በበኩላቸው ”ህዝብና መንግስት ውለው ይግቡ ባለቤቴ ከዘመተ ጀምሮ የሚደረግልኝ ድጋፍና ክብካቤ  ዘመድ ከሚያደርግልኝ በላይ ነው” ብለዋል፡፡

የማራኪ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፋሲል አብዩ፤  ክፍለ ከተማው ህዝቡን በማስተባበር የዘማች ቤተሰቦችን በመንከባከብና በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የዘማች ቤተሰብ የሆኑ 50 ህጻናት ነጻ ህክምና እንዲሁም 30 ህጻናት ደግሞ ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ክፍለ ከተማው ባለሀብቶችና ነዋሪዎችን በማስተባበር ዛሬ ለዘማች ቤተሰቦች ሩብ ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለእያንዳንዳቸው ከ3 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው፤ በከተማው የሚገኙ ማናቸውም የዘማች ቤተሰቦች  ሊቸገሩ አይገባም በሚል መርህ ያልተቋረጠ ድጋፍና ክብካቤ  እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለዘማች ቤተሰቦች ልጆች ነፃ የትምህርትና የህክምና አገልግሎት ከማመቻቸት ሌላ  የንግድና የመኖሪያ ቤቶች እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡