የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን አነቃቅቷል

74

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የህልውና ዘመቻውን በግንባር ተሰልፈው መምራት መጀመራቸው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን እንዳነቃቃው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምህር የሆኑት ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች አገር ስትሆን ከራሷ አልፎ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አፍሪካውያን ነጻ እንዲሆኑ በጽኑ ታግላለች፡፡

የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትም ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች፡፡

አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በማገዝ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የሆነችውን ኢትዮጵያን በማፍረስ አፍሪካን ለማዳከም ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በግንባር በመሰለፍ ይህንን ሴራ ለመመከት የሚደረገውን ትግል እየመሩ ሲሆን፤ ትግሉ የመላ ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን በመጥቀስ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡

በዚህ መሰረት አፍሪካውያን "#በቃ" ዘመቻን በመቀላቀል ለኢትዮጵያ ያለችውን አጋርነት በተግባር እያሳዩ ነው፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምህር የሆኑት ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት በስልጣን በቆየባቸው ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚያስችለውን እኩይ ሴራ ሲሰራ መቆየቱን ይናገራሉ።

አሸባሪ ህወሃት በትግራይ ስም የሚነግድና የኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ለማዳከም ለሚሰሩ ኃይሎች የሚላላክ ቡድን መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በግንባር መዝመታቸው ለመላው አፍሪካውያን ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርጊቱም የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን ዳግም ያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አፍሪካዊ በሆነ መንገድ የተነሳችበትን ጉዞ ለማደናቀፍ የተከፈተውን ጦርነት እየመከተች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የህልውና ትግሉ ዘረፈ ብዙ መልክ እንዳለው በማብራራት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ረገድ ከህዝብ የተቀበሉትን አደራ በብቃት እየተወጡ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም