የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለመጠባበቂያ ክምችት ከውጭና ከአገር ውስጥ የስንዴ ግዥ እየፈፀመ ነው

242

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በአገሪቷ ለመጠባበቂያ የእህል ክምችት ከውጭና ከአገር ውስጥ የስንዴና ሌሎች ምርቶችን ግዥ እየፈፀመ መሆኑን አስታወቀ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የስትራቴጂክ ሎጅስቲክስ ዘርፍ  ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሀሰን፣ አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ የሰብአዊ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው በቀጣይ በቂ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት እንዲኖር ከውጭና ከአገር ውስጥ የስንዴና ሌሎች ምርቶች ግዥ እየፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።

የግዥ ሂደቱ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከ400 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴ ከውጭ አገር ግዥው ተጠናቆ ወደ አገር ወስጥ የማስገባት ስራ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የብስኩት፣ የዱቄትና የሩዝ ምርት ግዥ ደግሞ በአገር ውስጥ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከውጭ ተጨማሪ 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመግዛት በሂደት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ።

በአገር ውስጥም በተመሳሳይ 117 ሺህ ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ምርቶች ግዥ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የመጠባበቂያ እህል ክምችት ግዥ በተጓዳኝ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እርዳታ ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በተለይ በአፋርና በአማራ ክልሎች  የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች ስላሉ በባህር ዳር እና ሰመራ በተቋቋሙት ጊዜያዊ የአስቸኳይ ማስተባበሪያ ማዕከላት ሰብአዊ ድጋፎች ተደራሽ እየሆኑ ነው ብለዋል።

መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በትግራይ ክልልም የሰብዓዊ ድጋፉ በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ምክትል ኮሚሺነሩ።

በጦርነቱ ሳቢያ ከተፈናቀሉ ዜጎች በተጨማሪ በድርቅና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም