ኦፕራሲዮን ነበርኩ ለሁለተኛ ጊዜ ሆዴን በጩቤ ሊቀዱት ሲሉ መከላከያ ደረሰልኝ

129

ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ኦፕራሲዮን ነበርኩ ለሁለተኛ ጊዜ ሆዴን በጩቤ ሊቀዱት ሲሉ መከላከያ ደረሰልኝ” በማለት የመዘዞ ከተማ ነዋሪ የሆኑት መምህር አለምሸት ተፈራ የአሸባሪውን ህወሃት የጭካኔ ጥግ ገለጹ።

የአሸባሪው ህወሃት ወራሪዎች ንጹሐንን በዱላ እንደሚቀጠቅጡም መምህር አለምሸት የደረሰባቸው መከራ አስከፊ መሆኑን አብራርተዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚያደርገውን የንጹሃን ግድያ፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት በሰሜን ሸዋ መዘዞ ከተማም ደግሞታል።

የሽብር ቡድኑ በጣርማበር ወረዳ መዘዞ ከተማ በቆየባቸው ቀናት ከዶሮ ጀምሮ የማህበረሰቡን እንስሳት እያረደ በልቷል።

በከተማዋ ያሉ ሱቆችን ሙሉ በሙሉ ዘርፎ የቀረውን አውድሟል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ፋኖና ሚሊሻ አባላትን ምት መቋቋም ተስኖት ሲፈረጥጥ ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉ ንጹሀንን በመግደል አረመኔነቱን አሳይቷል።

የመዘዞ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ መኮንን አበሩ እንዳሉት፤ ወደ ከተማዋ ከገቡ ጀምሮ የንግድ ቤቶችን በሀይል እየሰበሩ ንብረት ጭነው ወስደዋል።

እቤታቸው በተቀመጡበት የመሳሪያ አፈሙዝ ግንባራቸው ላይ ተደቅኖ ኪሳቸው እንደተበረበረና የያዙት ገንዘብ እንደተወሰደባቸውም ተናግረዋል።

ይህ ብቻ አይደለም ቤት ያፈራውን ሁሉ መብላት መጠጣታቸው አልበቃ ብሎ የሚደፈሩ ሴቶች እንዲያመጡላቸው በመጠየቅ ከፍተኛ ስቃይ የሚያደርስ ድብደባ ፈጽመውባቸዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ መምህር አለምሸት ተፈራ የደረሰባቸውን እንግልት ሲገልጹ "ሶስት ሆነው ወደ ቤቴ መጡ አንደኛው መሳሪያ አቀባብሎ ግንባሬ ላይ ደገነ፤ ሁለተኛው ሆዴ ላይ ጩቤ አነጣጠረ፣ ሽጉጥና ሌላ መሳሪያ አለህ አምጣ ሲል አስጨነቀኝ" ብለዋል።

“በሁለተኛው ቀን ከቤቴ ውስጥ እንዳለሁ ከውጭ ቆለፉብኝ በመስኮት ስወጣ በመሳሪያ እያስፈራሩ የዱላ መዓት አወረዱብኝ” ብለዋል።

በመዘዞ የቀድሞ የፖሊስ አባል የነበሩና በጡረታ የተገለሉ ግለሰብ በመኖሪያ ቤታቸው በር ላይ በጭካኔ ተገድለዋል።

በከተማዋ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶች አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆነው ወድመዋል፣ የተዘጉ ቤቶች በራቸው በሀይል ተከፍቶ እቃዎች ተዘርፈው የቀሩት አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ ተደርገው ተበታትነዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣_

መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም