በምዕራብ ሸዋ በመኸር ከለማው ሰብል ከግማሽ በላዩ ተሰበሰበ

224

አምቦ፣ ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኽር ወቅት ከለማው ሰብል ከግማሽ በላዩ መሰብሰቡን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከዞን እስከ ቀበሌ የአመራርና የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የደረሰ ሰብል ፈጥኖ እንዲሰበሰብ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።  

በጽህፈት ቤቱ የአዝርእት ልማት ባለሙያ አቶ ደጀኔ ገመቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በ2013/14 ምርት ዘመን መኽር ወቅት  607 ሺህ ሄክታር ማሳ ታርሶ በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል።

በምርት ወቅቱ ከለማው አጠቃላይ ማሳ እስካሁን  ከ315 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

የቤተሰብ ጉልበትና አደረጃጀቶችን በመጠቀም ከቀሪው ማሳ ላይ የሰብል ስብሰባው መቀጠሉን አመልክተዋል ።

የሀገር ሉአላዊነት ለማስከበር ወደ ግንባር ለዘመቱ የሚሊሻ አባላት ቤተሰቦችና ለአቅመ ደካሞችም በህብረተሰብ ተሳትፎ ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ እየተሰበሰበ ካለው የመኸር ሰብል ከ19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ባለሙያው አስታውቀዋል።

የአምቦ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር  አበራ ፊጡማ በበኩላቸው ነዋሪው የህልውና ዘመቻን ከመደገፍ ጎን ለጎን የደረሰ ሰብል በደቦ እየሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል ።

በግማሽ  ሄክታር ማሳ ላይ  ያለሙትን የደረሰ ስንዴ  ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመተባበር ሰብሰበው መከመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከስንዴ ጎን ለጎን  አንድ ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙትን ጤፍ፣ አተርና ባቄላ ወቅቱን ጠብቀው ለመሰብሰብ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

የደንዲ ወረዳ ኦሎንኮሚ አካባቢ ነዋሪ አርሶ አደር ሙለታ ደገፋ በበኩላቸው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ማሳቸው ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በሰው ሃይል ሰብላቸውን አጭደው እየከመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“የደረሰ ሰብል በጊዜ እንድንሰበስብና ላልደረሰ ሰብል ተገቢውን ጥንቃቄ እንድናደርግ በግብርና ባለሞያዎች ግንዛቤ አግኝተናል” ያሉት አርሶ አደር ሙለታ የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር ወደ ግንባር ለዘመቱ የሚሊሻ ቤተሰቦች ሰብልም እየሰበሰቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡