''ለኢትዮጵያ የምንሰስተው እውቀት፣ጊዜና ገንዘብ አይኖረንም ''

59

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22/2014(ኢዜአ) "ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ የምንሰስተው እውቀት፣ጊዜና ገንዘብ አይኖረንም" ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ትምህርት ክፍል ባለሙያዎች ገለጹ።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያ ጠል ከሆኑ የውጭ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አገር ለማፍረስ መጠነ ሰፊ ግፍ ቢፈጽምም የወጠነው ክፉ ሴራ በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የተባበረ ክንድ እየመከነ ይገኛል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በግንባር በመገኘት መከላከያ ሰራዊቱን ለመምራት ከዘመቱበት እለት አንስቶ መላው ኢትዮጵያዊያን መሪያቸውን በመከተል የአገርን ድል እያፋጠኑ ይገኛሉ።

በዛሬው እለትም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና  ትምህርት ክፍል በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ከ 1 ሚሊዮን 130 ሺህ በር በላይ የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ አድርገዋል።

በዚህም፣ 120 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ የተለያዩ አልባሳትና 100 ካርቶን የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ  ቁሶችን ለብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የደረት፣የልብና የአጠቃላይ ቀዶ ጥገና ሀኪም ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት "አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለመበታተን የያዘው ውጥን መቼም አይሳካም" ሲሉ ነው የተናገሩት።

የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ የምንሰስተው እውቀት፣ጊዜና ገንዘብ አይኖረንም ነው ያሉት፡፡

የሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ነብዩ ስዩም በተመሳሳይ የህልውና ትግሉ በድል እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅብንን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ  ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም