መላ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን ዘመናዊ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን ታግለው ነጻነቷ የተጠበቀ አህጉር መገንባት ይጠበቅቸዋል

74

ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) መላ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን የውጭ ጣልቃ ገብነትንና ዘመናዊ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን ታግለው ነጻነቷ የተጠበቀ አህጉር መገንባት እንደሚጠበቅባቸው ፖለቲከኛው ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ ገለጹ፡፡
ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ በተለየ መልኩ ዘመቻ እያካሄዱ ነው።

አገራቱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያውን አሸባሪ የህወሃት ቡድን በግልጽ በመደገፍ በመንግስት ላይ ጣልቃ ገብነትና ጫና እያደረሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ቡድን በተጨማሪ ከምዕራባዊያን አገራት እየደረሰባት ያለውን ሁሉን አቀፍ ዘመቻ በመመከት ላይ መሆኗን ኢንጅነር ዘለቀ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷም ባለፈ የመላ ጥቁር ህዝቦች የድል ተምሳሌት፤ የአፍሪካ የነፃነት ፋና ወጊ በመሆኗ ምእራባዊያኑ ታሪኳን የማደብዘዝ እቅድ እንዳላቸው ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ አሁንም ከራሷ አልፋ ለመላ አፍሪካ ነፃነት የምትታትር መሆኑንም እንዲሁ።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ክብሯንና ሉአላዊነቷን ለማስጠበቅ የያዘችው መንገድ መላ አፍሪካን ነጻ የሚያወጣ በመሆኑ ሁሉም  ከጎኗ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

ምዕራባዊያን አፍሪካ ውስጥ የህዝቦችን ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ የሀገሩን ሃብት በራሱ አቅም መጠቀምን የሚሻ እና ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም መሪ ማየት እንደማይፈልጉም ገልጸዋል፡፡

ለአገራቸው ቀን ከሌት የሚሰሩ አፍሪካዊያን መሪዎችን "አምባገነን" የሚል ስም ሲያጠፏቸው መቆየታቸውንም  ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የኮንጎውን ሉሙምባ እና የቡርኪናፋሶውን ቶማስ ሳንካራን በአርዓያነት ጠቅሰዋል፡፡

አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመቀም እያሳዩት ያለውን አጋርነት አድንቀው፤ ይህን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የህልውና ዘመቻውን በግንባር መምራት መጀመራቸው ለአገራቸው ህልውና የማይደራደሩ መሆኑን በተግባር ያሳየ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያዊያን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም