በደብረ ታቦር ከተማ ሉዓላዊነትን ለማስከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት የደም ልገሳ ዘመቻ 3 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ተሰበሰበ

98

ደብረ ታቦር ፤ህዳር 22/2014(ኢዜአ) በደብረ ታቦር ከተማ ሉዓላዊነትን ለማስከበር  እየተዋደቀ ለሚገኘው የፀጥታ አባላት የደም ልገሳ መርኃ ግብር   3 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ተሰበሰበ ።

የደም ባንኩ አገልግሎት  ኃላፊ አቶ ደጃች መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ለማስቀጠል እስከ ህይወት መስዋትነት እየከፈሉ ላሉ የፀጥታ አባላት ደም መለገስ ከሁሉም ይጠበቃል።

በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ደም በከተማው ከሚኖሩ በጎ ፈቃደኞች በዘመቻ ሲሰበሰብ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ወራት ውስጥም 2 ሺህ 750 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ በቅንጅት በተደረገ እንቅስቃሴ   3 ሺህ 238 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።

የተሰበሰበው ደም ለአስር የህክምና ተቋማት በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን አመልክተው፤ በአሁኑ ወቅትም በቂ የደም አቅርቦት ክምችት መኖሩን ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ የደም ባንኩ አገልግሎት ሰራተኞች በግንባር ለሚገኙ  የመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች  ስንቅ እያዘጋጁ ነው፡፡

ከደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ወይዘሮ አንጓች ደሳለኝ በሰጡት አስተያየት፤  አሁን ላይ በሁሉም ግንባር የህልውና ዘመቻውን ማገዝ ይገባል ብለዋል።

እርሳቸውም ለዘመቻው ድጋፍ የሚውል በፈቃደኝነት ደም  መለገሳቸውን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም በሚኖርበት አካባቢ  ሀብረተሰቡን አስተባብረው ገንዘብ በማሰባሰብ ለሰራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑንና ወደ ግንባር ለመዝመትም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በደም ባንኩ አገልግሎት የሂሳብ ሰራተኛ  ወይዘሮ ካሳዬ  ብዙአየሁ በበኩላቸው፤  ደም ከመለገሳቸው ባለፈ ዛሬ ለሰራዊቱ ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የደም ባንኩ አገልግሎት በተያዘው በጀት ዓመት ከ6 ሺህ ዩኒት በላይ ደም በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም