የኦሮሚያ ሴቶች አደረጃጀት ለክልሉ ፖሊስ አባላት ድጋፍ አደረገ

183

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22/2014(ኢዜአ) የኦሮሚያ ሴቶች ማኅበር፣ ሴቶች ፌዴሬሽንና ሴቶች ጉዳይ አደረጃጀት ለክልሉ የፖሊስ አባላት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረገ።

አደረጃጀቱ ከፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር በመተባበር ካደረገው ድጋፍ ሰንጋዎች፣ በሶ፣ ዳቦቆሎ እና የጽዳት ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

የኦሮሚያ ሴቶች ማኅበር ምክትል ሊቀ-መንበር ኮማንደር ሽቶ ዲቂሳ፤ አገሪቷ የገባችበት የህልውና ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን አደረጃጀቱ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉን ሴቶች ከወረዳ ጀምሮ በማነቃነቅ በስንቅ ዝግጅት፣ አካባቢን በመጠበቅ፣ በደም ልገሳና ዘመቻውን በመቀላቀል ጭምር ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።   

በሁለት ዙር ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅ መቅረቡን፤ በዚህም 9 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው 700 ኩንታል ስንቅ ባለፈው ሳምንት በተለያየ ግንባር መሰራጨቱን አክለዋል።

በዛሬው ድጋፍም ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ለተሰለፉ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት 15 ሰንጋዎች፣ በሶ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ ዘይት ሩዝና የጽዳት ቁሳቁስ አቅርበናል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት ሴቶችን በቁጭትና በወኔ ማነሳሳቱን ገልጸው፤ በሁሉም መስክ የምናደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሠላም እጦት ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶች ናቸው ያሉት ኮማንደር ሽቶ ለህልውና ዘመቻው ስኬት የሴቶች ተሳትፎ የበለጠ ሊጎላ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሽናሽ አቤቤ በበኩላቸው ዞኑ ከዘመቻው መጀመር አንስቶ ባለሃብቶችና ነዋሪዎችን በማስተባበር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በእስካሁን ሂደት ዞኑ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው 150 ሰንጋ በሬዎች፣ ፍየሎች፣ በጎችና ሌሎች ድጋፎችን ጠቅሰዋል።