በዓሉ አንድነትን በሚያጠናከሩና ሀገርን በሚያሻግሩ ዝግጅቶች ይከበራል- የፌዴሬሽን ምክር ቤት

80

ድሬዳዋ፤ ኅዳር 22/2014(ኢዜአ)16ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦና ሕዝቦች ቀን በዓል ሀገራዊ ለውጡን በሚያሻግሩና አንድነትን በሚያጠናክሩ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦና ሕዝቦች ቀን በዓል ዘንድሮ የሚከበረው በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነው።

ምክትል አፈ-ጉባኤዋ በዓሉን አስመልክተው በድሬዳዋ በሰጡት  መግለጫ እንደተናገሩት፤  የበዓሉ  መከበር ለውጡን ተከትሎ የተገኙ መልካም ተግባራት ለማስቀጠል፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት መንፈስን በፀና መሠረት ላይ ለማዋቀር ያግዛል፡፡

ሀገርን ለማዳን በየመስኩና በየግንባሩ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከር ልዩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

ሥራዎቹን በሚመለከትም ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡና ሲምፖዚየም እንደሚኖር አመልክተዋል፡፡

እንደ ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ገለጻ፤ የዘንድሮው በዓል በክልሎች ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ መሰናዶዎች፣ ለሠራዊቱ ደም በመለገስ፣ የዘማቾች ቤተሰቦችን በማገዝና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ ጭምር እየተከበረ ይገኛል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈቲያ አደም በበኩላቸው በዓሉ ''ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረው ሀገራዊ አንድነትንና የህልውና ዘመቻው በሚያስከብሩ ተግባራት ላይ አተኩሮ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

''በበዓሉ ላይ ጥላቻን አፍርሰን እውነተኛ የአንድነትን ድልድይ እንገነባለን'' ብለዋል፡፡

በዓሉ የሀገር ህልውና ለማስከበር በተጠናከረ አንድነት እንደ አድዋና ህዳሴ ግድብ ታሪክ ለመስራት የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ወይዘሮ ፈቲያ ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን ባከበረ ሁኔታ የፍቅርና የአንድነት ፣ የመዋደድና የመደጋገፍ እሴቶች መገለጫ በሆነችው ድሬዳዋ መከበሩ ኢትዮጵያዊ ህብረ-ብሔራዊነት ለማጽናት እንደሚያግዝ የገለጹት ደግሞ  የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው፡፡

በሀገሪቱ የህግ የበላይነት ከማስከበር ባሻገር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሰላምና በአንድነት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ያላቸውን ፍላጎት ለዓለም ማህበረሰብ የሚያሳዩበት ይሆናል ብለዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምከትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድና ልዑካን ቡድን ለበዓሉ በድሬዳዋ እየተከናወኑ  የሚገኙ ዝግጅቶችንና የበዓሉ ማክበሪያ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም