የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው መርህን መሰረት ያደረገ አቋም የሚደነቅ ነው

61

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው መርህን መሰረት ያደረገ አቋም የሚደነቅ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ላይ ከሚገኙት የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኋላ መግለጫ የሰጡት አቶ ደመቀ ከቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ገንቢና ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ ጉዳይ የያዘው መርህን መሰረት ያደረገና ቀጣይነት ያለው አቋም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቷን ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስቀጠል እየሰራ ያለውን ውጤታማ ስራ የቻይና መንግስት በቁርጠኝነት እየደገፈ ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የቻይና መንግስት ላሳየው ቁርጠኛ አቋም አድናቆት አለው ብለዋል አቶ ደመቀ።

ኢትዮጵያና ቻይና የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያም ይህንኑ ወዳጅነት ታጠናክራለች ነው ያሉት።

የቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ በበኩላቸው ቻይና በሉዓላዊ አገር ጣልቃ መግባት ፍላጎት የሌላት አገር ናት ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ጋርም በጽኑ መሰረት ላይ የቆመ ጠንካራ ግንኙነት መስርታ የኖረች አገር ናትም ብለዋል።

ይህ ግንኙነት እንዲቀጥል ቻይና የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንደምታደርግም ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ቻይናውያንና የልማት ስራዎቻቸው ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጥርጥር እንደሌላቸውም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም