የልደታ ክፍለ ከተማ ለሰራዊቱና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

72

ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የልደታ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊትና በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ተፈናቅለው በደብረብርሃን ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ለመታደግ እየተፋለመ ያለውን የመከላከያ ሰራዊት መደገፍ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡

ክፍለ ከተማው ለሰራዊቱ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ክፍለ ከተማው ለሰራዊቱና በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ተፈናቅለው ደብረብርሃን ለሚገኙ ዜጎች 20 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ እስካሁን ከ5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም የሚጠበቅበትን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

ድጋፉን የተቀበሉት የመከላከያ ሰራዊት ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ለቺሳ መገርሳ የህዝቡ ድጋፍ ለሰራዊቱ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ገልጸው፣ ህዝቡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ደጀንነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም