ዳያስፖራዎች ለሁለት ሆስፒታሎች ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መገልገያዎች ድጋፍ አደረጉ

117

ደብረ ታቦር ህዳር 21/2014(ኢዜአ) በአሜሪካና በካናዳ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ለንፋስ መውጫና መቄት ሆስፒታሎች ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አደረጉ፡፡
ለንፋስ መውጫና መቄት ሆስፒታሎች የተደረገው ድጋፍ 100 አልጋዎች፤ 100 ፍራሾችና የሕክምና መገልገያ እንደሚያካትት በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።  

የድጋፉ አስተባባሪ ዶክተር አዳሙ አንለይ  በዚሁ ወቅት ድጋፉ  በሁለቱ ሀገሮች የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን በማስተባበር መሰባሰቡን ተናግረዋል።

አሸባሪውና ወራሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተጎዱት ሁለቱ ሆስፒታሎች የገጠማቸውን የሕክምና መገልገያዎች ጉድለት ለመሙላት ጥረቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው ሆስፒታሎቹ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መልሰው በመቋቋም ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን በሆስፒታሎቹ  ያደረሰውን ጥፋት መጠን በጥናት በመለየት ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ ዳያስፖራውና ሌሎችን አካላት በማስተባበር በፍጥነት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን አስታውቀዋል።

ድጋፉ ሆስፒታሎቹ አገልግሎታቸውን በተሻለ መልኩ ለመስጠት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ሆስፒታሎቹ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘው የንፋስ መውጫና በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው የመቄት ሆስፒታሎች በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ውድመት እንደደረሰባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም