የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሰላሳ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ

158

ጅማ፤ ህዳር 21/2014(ኢዜአ) የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከደመወዛቸው በመቀነስ ከሰላሳ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ወስኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ  አባላት  በማህበራዊ የትስስር ገፆች አጠቃቀም ዙሪያ በሚስተዋሉ  ችግሮችና መፍትሄያቸው ዙሪያ ተወያይተዋል።

በመጀመሪያው ዙር የድጋፍ አሰባሰብ  የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከደመወዙ 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንና ዛሬ የወሰነው ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ   ለመለገስ መወሰኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሀገርን ከጠላት ወረራ ለመከላከል በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል እየሰራ መሆኑን ተናገረዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ በበኩላቸው ” ከደመወዜ በመቁረጥ  ድጋፍ ማድረግ ሀገር ካለችበት ችግር አንጻር ባጣም ጥቂት አስተዋጽኦ ነው” ብለዋል፡፡

’’ህይወቱን የሚገብር ቤት ንብረቱን ልጆቹን ጥሎ ለሀገር ህልውና ዋጋ የሚከፍል እያለ እኛ የደመወዛችንን የተወሰነ መጠን  መስጠት ቀላል መሆኑን ነው  ዶክተር ደመላሽ የገለጹት፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ መምህር በላይ በየነ በበኩላቸው “ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ የምንረዳ በመሆኑ ለሚደረገው ሀገር የማዳን ተጋድሎ ሁሉ የበኩሌን  ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል፡፡

ገንዘብ ከማሰባሰብና የወጡ ህግጋትን ከማክበር ባሻገር በየትኛውም ሀገር የማዳን ተግባር ላይ የበኩላችንን ለመወጣት ወደ ኋላ እንደማይሉም አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ስታፍም ሆነ ማንኛውም ግለሰብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከሉ ድርጊቶችን ከመፈፀም እንዲታቀቡ የዩኒቨርሲቲው የህግ ክፍል ሀላፊ አቶ ዮሴፍ አለሙ አሳስበዋል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ከቅንነት በመነጨ ይጠቅማል ብለው ያሰቡትን የጦር ግንባር ድሎችን ጨምሮ መዘገብና በማህበራዊ የትስስር ገፆች  ሆነ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨት የተከለከለ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ብለዋል፡፡

የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅና ተመሳስለው የሚገቡ የጠላት ተላላኪዎችን ለመከላከል ሲባል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ማክበርና ማስከበር   የሁሉም ሰው ግዴታ ነው ብለዋል አቶ ዮሴፍ፡፡