የሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ተጠርጣሪ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

68
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 ፖሊስ በሰኔ 16 የቦምብ ጥቃት ተጠርጥረው ምርመራ ላይ የሚገኙት አቶ ተስፋዬ ኡርጌን በተመለከተ የጠየቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ በፍርድ ቤቱ ተፈቀደለት። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ማስተባበሪያ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው በሰኔ 16 መስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ በወጣው ህዝብ ላይ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት አስተባብረዋል በሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ባሉ ሁከቶችና ብጥብጦች እጃቸው እንዳለበት ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል። በዚህ መሰረት መርማሪ ፖሊስ አቶ ተስፋዬ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊቶች አፈጻጸማቸው ውስብስብና አዳጋች በመሆኑ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቋል። እንዲሁም ሌሎች ግብረ-አበሮች ሊኖሩ ስለሚችሉና ተጨማሪ የምስክር ቃል ተቀብሎ ባለመጨረሱ መሆኑን ነው መርማሪ ፖሊስ ያስታወቀው። ተጠርጣሪው በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮዎች የወሰደ ቢሆንም ምርመራውን ማጠናቀቅ ሲገባው ባለማጠናቀቁ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜው ሊፈቀድ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። ስለሆነም የዋስትና መብቴ ተከብሮ ጉዳዬን በውጭ ሆኜ እንድከራከር ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጥልኝ ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰቱ ግጭቶች እጃቸው አለበት ለተባለውም ችግሮች እየተፈጠሩ የነበረው ተጠርጥሬ ከተያዝኩ በኋላ በመሆኑ ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው በዋስትና ቢወጡ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን ሊያሸሹ ስለሚችሉ የዋስትና መብቱን ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ወንጀል ከባድና የሰው ህይወት ያለፈበት በመሆኑ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎችን እንዲያደርግ የተጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። በዚህም መሰረት ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓ.ም ከጥዋቱ 4 ሰዓት መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም