''ለሀገር ኩራት ከሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች ጋር በግንባር ተገኝቼ በሙያዬ ማገልገልን ናፍቄያለሁ''-ሲስተር ራሄል ዓባይ

87

ዲላ ህዳር 21/2014 (ኢዜአ)''ለሀገር ኩራት ከሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች ጋር በግንባር ተገኝቼ በሙያዬ ማገልገልን ናፍቄያለሁ''የሚሉት ሲስተር ራሄል ዓባይ ናቸው።
ሲስተር ራሄል ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር ወደ ጦር ግንባር ሄደው ከጠላት ጋር እየተፋለሙ ያሉ ጀግኖቻችንን በሙያቸው የማገልግል ፅኑ ፍላጎት አላቸው።

የሀገሪቱ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በግንባር እየተፋለሙ ባሉበት በሞቀ ቤት መቀመጥ ዕረፍት እንደነሳቸውም ተናግረዋል።

ጀግኖች በጦር ግንባር ጠላትን በሚያደባዩት በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ ልጆች ጎን ሆነው በሙያቸው ማገልገል እንደናፈቁ ሲስተር ራሄል ገልጸዋል።

"ቤተሰቦቼ በሰላምና በነፃነት የሚኖሩት ሀገር ስትኖር ነው" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

''ሀገርን ለማዳን በግንባር ከሚፋለሙ መካከል መሆን ትልቅ ክብር ከመሆኑ በተጓዳኝ የዚህ ታሪካዊ ትውልድ አካል በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል'' ያሉት ደግሞ  የጤና ባለሙያ አቶ ደስታው ሞገስ ናቸው።

ሠራዊቱን በሙያቸው ከማገልገል ባለፈ ጠላትን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

''ለሀገር ጥሪ ምላሽ መስጠት ትልቅ ደስታ ይፈጥራል'' ያሉት የዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል የህክምናና ተግባር ስልጠና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደረጀ ዳንኤል ናቸው።

ዶክተር ደረጀ፣የሆስፒታሉ በርካታ ባለሙያዎች ለሀገር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ''ለሀገር ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠታችሁ ልዩ ክብር ይገባችኋል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም