ሀገርን ለማዳን እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የጋራ ምከር ቤቱ አባላት

71

ሐረር፤ ህዳር 21 ቀን 2014(ኢዜአ) ሀገርን ለማዳን በግንባር እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ሰራዊት ለመደገፍ በሚደረገው ሁሉ አስተዋጽኦዋቸውን እንደሚያጠናክሩ የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት አስታወቀ።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት "ደሜ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት” በሚል ዛሬ ደም ለግሰዋል።

ወይዘሮ ሐሰናት ሙሜ ከጋራ ምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዷ ሲሆኑ፤ ለሀገር ህልውና መከበር  ህይወቱን አሳልፎ እየሰጠ ላለው መከላከያ ሰራዊት ደም ሲሰጡ በደስታ መሆኑን ተናግረዋል።

እሳቸው የለገሱት ደም  ሰራዊቱ እየከፈለ ካለው መስዋትነት ጋር ሲነጻጸር ትንሽ መሆኑን ጠቅሰው፤  የደጀንነት ድጋፋቸውን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚካሄደው እንቅስቅሴ በመሳተፍ የድርሻቸውን  እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ሌላው የጋራ ምክር ቤቱ አባል አቶ አዝማች ጌጡ በበኩላቸው፤ በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ደጀን መሆናችንን ለማሳየት የደም ልገሳ እያደረኩኝ እገኛለሁ ብለዋል።

በቀጣይም የአካባቢውን  ሰላም ለማረጋገጥ ከሚያደርጉት ተሳትፎ በተጨማሪ ሀገርን ለማዳን እየተዋደቀ ለሚገኘው ለጀግናው መከላከያ ሰራዊትን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

ብረት አዝሎ ተራራ በመወጣት  ጠላትን ለማጥፋት እስከ ህይወት መስዋትነት እየከፈለ ላለው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት  የሚያስፈልገውን እየደገፍን አለኝታችንን እያሳየን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የጋራ ምክር ቤቱ  አባል አቶ ሄኖክ ሀይሉ ናቸው።

ሁሉንም ማድረግ የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው   የሚሉት  አቶ ሄኖክ፤ ባለኝ አቅም ሁሉ ሰራዊቱን ለመደገፍ እና ሀገርን ለማዳን  የበኩሌን አደርጋለው ሲሉ አረጋግጠዋል።

አቶ ሃምዛ ሽመልስ በበኩላቸው፤  በመከላከያ ሰራዊት ህይወት ውስጥ እንደማለፌ ለእኔ መከላከያ ሰራዊት ጀግና እና ለሰንደቅ ዓላማው  ሲል ህይወቱን የሚሰጥ ነው፤ የሀገር ባለውለታም ነው ብለዋል።

 ለዚህ ሰራዊት በሚደረገው ሁሉ ግንባር ቀደም ሆኜ ለመሰለፍ እና ያለኝን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ ሲሉ አስታውቀዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ሀሰን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና ደጋፊዎችን እንዲሁም ህብረተሰቡ ሀገርን  ለማዳን እየተካሄደ ባለው እንቅስቀሴ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የበኩላችንን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዛሬም አባላቱ የደም ልገሳ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም