የጋምቤላ ክልል ሕዝብ ለሕልውና ዘመቻው ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል ሕዝብ ለሕልውና ዘመቻው ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

ህዳር 21/2014/ኢዜአ/ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁለ ''ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር በሀገር ላይ የተደቀነውን ወቅታዊ አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት የክልሉ ህዝብ ሁሉን አቀፍ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል '' አሉ።
የጋምቤላ ክልል ህዝብ የሕልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ አስገነዘቡ።
‘’ወንድማማችነት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሃሳብ 16ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በክልል ደረጃ በጎደሬ ወረዳ ተከብሯል።
ርዕሰ መሰተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓትና ተላላኪዎች በኢትዮጵያ ላይ የደቀኑትን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
የሽብር ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲፈጽም የቆየውን ግፍና በደል አልበቃው ብሎ አሁንም ሀገር ለማፍረስ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም የሽብር ቡድኑ 'እኔ ያልመራኋት ሀገር መፍረስ አለባት’ በሚል ከታሪካዊ ጥላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተቻለውን ሁሉ እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ቀን በዓልን የሽብር ቡድኑ ዜጎችን ከፋፍሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሊጠቀምበት እንዳሰብው አልተሳካለትም ብለዋል።
ይልቁንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ውንድማማችነትን ያጠናከሩበት መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የብሄሮችና ብሄረሰቦች በዓል ልዩ የሚያደርገው የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የቀደምት መሪዎችን ታሪክ በደገሙበት ወቅት መሆኑ ነው።
የክልሉ አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ሁሉም አንድነቱ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
የህልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ጎን ለጎን በክልሉ ለተጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች ስኬትም የክልሉ ህዝብ ጠንክሮ እንዲሰራ አሳስበዋል።
የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው በግንባር እየተፋለሙ ላሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች የጀመሩትን ህዝባዊ ደጀንነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
16ኛው የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በፓናል ውይይትና በአደባባይ ህብር ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በክልል ደረጃ በጎደሬ ወረዳ ላለፉት ሁለት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።