የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል

259

ህዳር 21/2014/ኢዜአ/ ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
በዓሉ "የአካል ጉዳተኞችን መሪነትና ተሳትፎን ለማረጋገጥ አካታች፣ተደራሽና ዘላቂ ድህረ-ኮቪድ-19 ዓለም እንገንባ'' በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እለቱን    አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ የዘንድሮው የአካል ጉዳተኞች ቀን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደሚከበር ጠቁመው፤ በእለቱም የአካል ጉዳተኞች መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚነሱበት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያወጣቸው ህጎችና መመሪያዎች እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አመዲን  በበኩላቸው አካል ጉዳት የእለት ተእለት ክስተትና አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግስት አካል ጉዳተኞችን ማካተትና ማሳተፍ ላይ ትኩረት እድርጎ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ አካል ጉዳተኞች በመምረጥ፣ በእጩነት እና በመታዘብ መሳተፋቸውን አስታውሰው፤ በመንግስት መዋቅር ወስጥ በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነት እንዲሳተፉ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የአካል ጉዳተኞች ሁሉን አቀፍ ረቂቅ ህግ መንግስት በዘርፉ የተሻሉ ስራዎችን እንዲያከናውን እድል እንደሚፈጥርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ህዝብ መካከል ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የአካል ጉዳት እንዳለባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።  

የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በየዓመቱ ህዳር 24 ቀን የሚከበር ሲሆን፤ ዘንድሮም በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም