በዱባይ 2020 ኤክስፖ ኢትዮጵያ ይዛ የቀረበቻቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በ200 ሺህ ሰዎች ተጎብኝተዋል

69

ኅዳር 21/2014(ኢዜአ) በዱባይ 2020 ኤክስፖ ባለፉት ሁለት ወራት 200 ሺህ ሰዎች ኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች መጎብኘታቸውን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በኤክስፖው የተሳተፉ 17 ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውንም ነው የገለጸው፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስር የኤክስፖ 2020 ዱባይ ኮሚሽን የኤክስፖውን የሁለት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህ ወቅት ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አሰፋ ሙሉጌታ እንዳሉት፤ በኤክስፖው ኢትዮጵያ የሰው ዘርና የቡና መገኛ፣ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሁም ምቹ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል።

ኢትዮጵያ የሉሲ ቅሪተ አካልን፣ ባህላዊ የቡና አፈላል ስነ-ስርዓትና ያሏትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በኤክስፖው በተሰጣት ስፍራ (ፓቪሊዮን) ለእይታ ማቅረቧንም ተናግረዋል።

ኤክስፖው ከተጀመረበት እ.አ.አ ከኦክቶበር 1ቀን 2021 ጀምሮ ባሉት ሁለት ወራት የኢትዮጵያ ይዛው የቀረበችው ምርትና አገልግሎት በ200 ሺህ ጎብኚዎች መታየን ገልፀዋል።

በኤክስፖው የተሳተፉ 17 ድርጅቶችም በአገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 3 ሺህ 800 ስዎች ደግሞ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ፍላጎት ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

 ኢትዮጵያ በኤክስፖው እያደረገች ያለችው ተሳትፎ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኤክስፖው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶችን  መጎብኘታቸውንም ገልፀዋል።

የኤክስፖው አዘጋጆች በዱባይ ካለው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ባህልና እሴት በሚያሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ቀንን ማክበራቸውን ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ አራት ወራትም በኤክስፖው የኢትዮጵያን ገፅታ እንዲሁም የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቁ ስራተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በኤክስፖው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለፃ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጎብኚዎቹ ኢትዮጵያ የገጠማት ጊዜያዊ ችግር መሆኑን እንደሚገነዘቡና ኢትዮጵያን ለመጎብኘትና ኢንቨስት ለማድረግ  ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸውን ተናግረዋል።

በኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን መልክዓ ምድራዊና የተፈጥሮ ሃብቶች እንዲሁም የራሷ ቁጥርና ፊደል ባለቤት መሆኗን የሚገልጽ የተለየ ክፍል አላት።

የኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚ አማራጮቿን እንዲሁም የቡና አፈላል ስነ-ስርዓት የሚያሳይ ክፍል መኖሩም ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ፊደላት ልጆች ስማቸውን የሚፅፉበትን ጨምሮ ሌሎች መጫወቻዎችን የያዘ ክፍል መኖሩም እንዲሁ፡፡

ኤክስፖው ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን፤ በቀጣይም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚካሄድ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በኩባ ሀቫና፤ በቻይና ሻንጋይ እና በጣሊያን ሚላን ከተሞች በተካሄዱ ኤክስፖዎች ተሳታፊ እንደነበረች ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም