ለህልውና ዘመቻው ስንቅ ዝግጅት ባለፈ ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅተናል

89

ጎንደር፤ ህዳር 21/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ ለህይወታቸው ሳይሳሱ ቆርጠው ለዘመቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከስንቅ ዝግጅት ባለፈ ወደ ግንባርም ለመዝመት መዘጋጀታቸውን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጯኺት ከተማ የመንግስት ሠራተኞች አሰታወቁ፡፡
የመንግስትን የክተት ጥሪ ተከትሎ የዞኑ ህዝብ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

በከተማው በመንግስት ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ አባይነሽ ደጉ፤  ከዚህ ቀደም የወር ደመወዛቸውን በመስጠት ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ ማድረጋቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቅድሚያ ለሀገሬና ለህዝቤ ብልው ወደግንባር መዝመታቸው የደጀንነት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲወጡ ያነሳሳቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

"የሰላም አየር አግኝተን ሥራችንን ለማከናወን የቻልነው ሌሎች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ስለከፈሉን ነው'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ለምለም ተክሉ ናቸው፡፡

''ከጠላት ጋር ተናንቆ ውድ ህይወቱን እየከፈለ ላለው መከላከያ ሠራዊታችን ስንቅ አዘጋጅቶ መላክ ብቻ ሳይሆን በግንባር አብሬው በመሰለፍ መስዋዕትነት ለመክፈል ለህይወቴ አልሳሳም'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የመንግስት ሠራተኛ አቶ መኳንንት ጥበቡ፤  "በርካታ የሥራ ባልደረቦቼ ሀገር ከሌለ ሰርቶ መኖርም ሆነ በሰላም ወጥቶ መግባት የለም በሚል ዘምተዋል፤ እኔም የባልደረቦቼንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርዓያነት ለመከተል ተዘጋጅቺያለሁ" ብለዋል።

"በተለይ የዶክተር አብይ አህመድ በግንባር መዝመት ለዚህ ትውልድ አዲስ ታሪክ ከማሳየት በላይ በግንባር ያለውን ሠራዊት እና በደጀንነት የተሰለፈውን ህዝብ በእጅጉ አኩርቷል፤ አነሳስቷል" ብለዋል።

"የጯኺት ከተማ ነዋሪዎች ሀብት፣ ንብረት እና ገንዘብ ከሀገር ህልውና አይበልጥም" በሚል ከስንቅ ዝግጅት ባለፈ ሁለት ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ማዋጣታቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው የሀብት አፈላላጊ ኮሜቴ ሰብሳቢ አቶ ደረሰኝ ተስፋ ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደግንባር መዝመት ተከትሎ እየተሰማ ያለው የድል ዜና በደጀንነት እየተንቀሳቀሰ ያለውን ህዝብ እንደ አዲስ ማነሳሳቱን ተናገረዋል።

"ጦርነቱ በድል እስኪጠናቀቅ ድርስ የስንቅ ዝግጅቱም ሆነ የሃብት ማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡ 

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሀብት አሰባሳቢ  ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አይቸው ታረቀኝ እንዳሉት፤ ህዝቡ ለህልውና ዘመቻው እያሳየ ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ በእጅጉ የሚያኮረና ለድሉ መፋጠን ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው፡፡ 

የዞኑ ህዝብ ለክተት ጥሪው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠትም  ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም 77 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ስንቅ በማዘጋጀት ግንባር ድረስ ሄዶ ለሠራዊቱ ማስረከብ እንደቻለ ጠቅሰዋል።

እስካሁንም 500 ኩንታል ደረቅ ስንቅ በማዘጋጀት ለሠራዊቱ በግንባር እንዲደርስ የተደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 780 ኩንታል ስንቅ መዘጋጀቱም ተመልክቷል።

ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት በስንቅ ዝግጅቱና በሃብት የማሰባሰቡ ስራ እስከ ድሉ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አይቸው ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም