ድርጅቶቹ ዜጎችን ለመደገፍ ያሳዩት ቸልተኝነት መርኋቸውን የተጻረረ ነው--የህግ ምሁራን

121

ባህር ዳር ህዳር 21/2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ዜጎችን በመደገፍ በኩል ያሳዩት ቸልተኝነት የሰብአዊ እርዳታ መርሆዎችን የሚጻረር ነው ሲሉ የህግ ምሁራን አመለከቱ።

ምሁራኑ አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው የአማራ አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ በምግብና በመድሃኒት እጥረት እየደረሰ ያለውን ጉዳት አስመልክተው ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአማራ ክልል የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት የህግ ተመራማሪ አቶ ይማም ሰይድ እንዳሉት ህወሀት በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ንጹሀን ዜጎች ለሞትና ለአስከፊ ሰቆቃ እየተዳረጉ ነው።

"አሸባሪው ህወሀት በወረራቸው አካባቢዎች ዜጎች የምግብ፣ የመድሃኒትና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማግኘት ባለመቻላቸው በርካቶች ለሞት ተዳርገዋል" ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የተቋቋሙት በሰብአዊነት፣ ገለልተኛና ከአድሎ በጸዳ መልኩ በጦርነት ውስጥም ገብተው እርዳታ ማቅረብ ቢሆንም ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን አመልክተዋል።

አቶ ይማም እንዳሉት ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ግጭት ውስጥ ገብተው ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ሰጥተዋል።

"አሁን ላይ አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው  የአማራና አፋር አካባቢዎች ዜጎች ከአራት ወር በላይ በሶቆቃ ውስጥ  ቢሆኑም ችላ መባላቸው ድርጅቶቹን ትዝብት ውስጥ ከቷቸዋል" ብለዋል።

"ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ መርሆዎች ውስጥ አንዱ በጦርነት ውስጥም ቢሆን ገብቶ ሰብአዊ እርዳታ መስጠት ነው" ያሉት አቶ ይማም "ይህን አለማድረግ መርሆዎቹን መጣስ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል።

አቶ ኢማም እንዳሉት ተራድኦ ድርጅቶቹ እየፈጸሙ ያለው ፍትሀዊነት የጎደለው ድርጊት የሚያመላክተው ፍላጎታቸው ለንጹሃን የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ ብቻ ሳይሆን ሌላ ተልዕኮ እንዳላቸው ነው።

ድርጅቶቹ ቀደም ሲል ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ ከጫኑ 70 በመቶ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች አለመመለሳቸውን እያወቁ  አሸባሪውን ህወሓት ሲጠይቁም ሆነ ሲያወግዙ አለመደመጣቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

"የድርጅቶቹ ዝምታ አሸባሪው ህወሀት የዓለም አቀፍ ህግን በመጻረር ተሽከርካሪዎቹን ለሠራዊትና የጦር መሳሪያ መጫኛነት በመጠቀም በንጹሃን ላይ ግፍ እንዲፈጽም መፍቀዳቸውን ያሳያል" ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ዳይሬክተር አቶ አበበ ካሴ በበኩላቸው ሰብአዊ እርዳታ ከብሔር፣ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከሌሎች ጉዳዮች በጸዳ መልኩ የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

"ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች አንዳንዴ የራሳቸውንና የገንዘብ ምንጫቸውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከመርሁ አፈንግጠው ሲንቀሳቀሱ ይታያል" ብለዋል።

የተራድኦ ድርጅቶቹ  እንደ አገርና ህዝብ የሚፈጽሙትን አድሎ ለመቀነስ እውነታውን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው በተናበበ መልኩ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

አቶ አበበ እንዳሉት በአሸባሪው ህወሀት የተከሰተውን የጉዳት መጠንና የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ እንዲሁም እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና በማስገንዘብ ድርጅቶቹ አቋማቸውን እንዲቀይሩ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ሽብርተኛው ህወሀት በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ መንግስት የጀመረውን የህልውና ዘመቻ በሁሉም ግንባሮች አጠናክሮ በማስቀጠል አካባቢዎቹን ፈጥኖ ነጻ ማውጣት እንደሚገባ የህግ ምሁራኑ አመልክተዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅርብ መረጃ እንደሚያሳየው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ7 ሚሊዮን በላይ ንጹሀን ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም