ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር የሚመሩት የህልውና ዘመቻ የላቀ ድል እየተመዘገበበት ነው

259


አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2014 (ኢዜአ) ”ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር የሚመሩት የህልውና ዘመቻ የላቀ ድል እየተመዘገበበት ነው” ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህልውና ዘመቻ ተሳትፎ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ የአገሪቷ ወቅታዊ የጽጥታ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት በጽህፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የአገሪቷን አንድነት ለማስቀጠል በግንባር ሆነው አመራር እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የተደቀነውን ስጋት የመመከቱ ተግባር ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች በአሸባሪው ሕወሓት ተይዘው የነበሩ ስፍራዎችን እያስለቀቁ መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም አሸባሪው ህወሃት አስገድዶ ያሰለፋቸው የትግራይ ወጣቶች ጦርነቱ እያለቀ መሆኑን ተገንዝበው ለመንግስት ጸጥታ ሃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡም ጥሪ መቅረቡንም አስታውሰዋል።
የስብዓዊ እርዳታን በተመለከተም በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አማካኝነት ለአማራ፣ ለአፋርና ለትግራይ ክልል እርዳታ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባራው ሕወሓት በአማራ ክልል ከ 1 ነጥብ 1 ሚሊዬን በላይ ሰዎችን ከቀያቸው ያፈናቀለ ሲሆን በአፋር ደግሞ ከ100 ሺዎች በላይ ተፈናቅለዋል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል አንዳንድ አካላት በኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግስትን ለመለወጥ የተለያዩ እኩይ ስራዎችን እየሰሩ ነው ብለዋል።
በአገሪቷ ሁሉም አከባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዳለ አስመስሎ ማቅረብ የዚሁ ሴራ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርጊቱም መሬት ላይ ያለውን እውነት የካደና ኃላፊነት የጎደለው መሆኑን ተናግረዋል።
የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ የውስጥ ይሁን የውጪ አካላት ከድርጊታቸው ሊቀጠቡ እንደሚገባም አስጠንቅቀዋል።
በመደበኛም ይሁን በማህበራዊ ሚዲያ ሆን ብለው የተዛባ መረጃ እያሰራጩ ያሉ አካላትም ከዚሁ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
ዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊ መልኩ ከተመረጠ መንግስት ጋር በትክክለኛው መንገድ መስራት እንዳለባቸውም እንዲሁ።
በተለያ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ የዲያስፖራ አባላት የኢትዮጵያውን እውነታ ለማሳወቅ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።