በኢትዮጵያ የገበያና የምርት ስብጥር መዳረሻ አገራትን በማስፋት ከገበያ የሚያስወጡ አገሮችን ጫና መቋቋም ይቻላል

88

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉ የገበያና የምርት ስብጥር መዳረሻ አገራትን በማስፋት "የእኛን አጀንዳ ካልፈጸማችሁ" በማለት ከገበያ የሚያስወጡ አገሮችን ጫና መቋቋም እንደሚቻል የዘርፉ ምሁራንና ተመራማሪዎች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ተዋፅኦዎችን እሴት ጨምራ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የማግኘት ሰፊ እድል ያላት መሆኑንም ነው የገለጹት። 


በአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ማእከል ተመራማሪ ዶክተር ወርቅነህ አያሌው፤ በኢትዮጵያ በተለይም የእንስሳት ሃብት ዘላቂ ልማት፣ የስራ እድልና ሰፊ የገበያ እድል የሚፈጥር ዘርፍ መሆኑን ያስረዳሉ።

በአነስተኛና ከፍተኛ ደረጃ የመልማት አቅም ያለውን የንብ ማነብ ስራ በጥራት፣ በብዛትና በተወዳዳሪነት ማከናወን ከተቻለ የማይቋረጥ የገበያ ተፈላጊነት ያለው ልማት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በንብ ማነብ ስራ በርካታ ዜጎችን በማሳተፍና ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ምንዛሬ የሚገኝበት ጥሩ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የግብርና ልማትና የተፈጥሮ ሃብት በዘመናዊ መልኩ በማልማት ለገበያ ማቅረብ ከቻለች ስኬታማ መሆኗ እርግጥ እንደሚሆን ዶክተር ወርቅነህ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በቆዳና ሌጦ ያላትን ሃብት እሴት በመጨመር በጥራት ለውጪ ገበያ ማቅረብ ከቻለችም ሌላው ከፍ ያለ ገቢ የምታገኝበት ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግብርና ምርምርና ልማት ባለሙያው ዶክተር ጸደቀ አባተ፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸው የግብርና ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ መሆኑን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ እስካሁን ወደ ውጭ እየተላኩ ካሉት የግብርና ተዋጽኦዎች 92 በመቶው እሴት ሳይጨመርባቸው የሚላኩ ናቸው ይላሉ።

በተፈጥሯቸው እሴት ሳይጨመርባቸው ለገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ቢኖሩም ጥራትን ማስጠበቅና እሴት የሚያሻቸው ላይ ጨምሮና አሻሽሎ ለገበያ ማቅረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የግብርና እና እንስሳት ሃብት ልማት ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የውጪ ምንዛሬ ልታገኝባቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ያብራራሉ።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ180 በላይ የተለያዩ የሰብል አይነቶችን ለውጪ ገበያ የምታቀርብ መሆኑን ዶክተር ጸደቀ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ከሆኑ አገሮች መካከል ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ሳኡዲ አረቢያና ሌሎችንም ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም