ኪነ ጥበብ የምትቀጥለው ሀገር ስትኖር ነው – ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን

154

ክልል ህዳር 21/2014 (ኢዜአ) እኛ ኖረን ኪነ ጥበብን ማስቀጠል የምንችለው ሀገር ስትኖር በመሆኑ የሀገራችንን ህልውና እናስከብራለን ሲሉ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን አስታወቁ።
 ኪነጥበብ በሀገር ግንባታ ያለውን አስተዋጾ በመጠቀም የዘርፉ ባለሙያዎች በህልውና ዘመቻው ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመላክቷል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እንዲሁም  የኦሮሞ ባህል ማዕከልና  የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሰራተኞችና አመራሮች በወቅታዊ አገር ጉዳይ በመምከር ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል ።

የተቋማቱ አመራሮችና ሰራተኞች በአገር ግንባታ የኪነጥበቡ ዘርፍ ሚና በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በኦሮሞ ባህል ማዕከል መክረዋል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ ከውጭና በውስጥ ጠላቶቿ ለጥቃት ተጋልጣ ባለችበት በዚህ ወቅት ከኪነጥበቡና ከዘርፉ ባለሙያዎች ምን ይጠበቃል? የሚጠበቅብንን ድርሻስ እንዴት መወጣት ይገባል? በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተኮረ የጥናት ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል ።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን በወቅቱ ባደረጉት ንግግር አሸባሪው ህወሀት ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር በሀገር ህልውና ላይ ጦርነት ከፍቷል ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች በሀገር ላይ የተቃጣውን ጦርነት ለመመከት የህይወት መስዋእትነት እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

“ጠቅላይ ሚኒስትራችንና አመራሮቻችንም ግንባር ድረስ በመዝመት  አሸባሪውን ህወሃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጥፋት ድርጊቱ ለመመከት በመፋለም ላይ ባሉበት በዚህ ጊዜ አርፈን የምንቀመጥበት ምክንያት አይኖርም ” ሲሉ ተናግረዋል ።

ኪነ ጥበብ የምትቀጥለውም ሆነ እኛም እንደ ህዝብ መኖር የምንችለው ሀገር ስትኖር ነው” ያሉት ወይዘሮ ሰዓዳ “ከምንም ነገር በፊት የሀገራችንን ህልውና እናሰከብራለን” ብለዋል  ።

ኪነ ጥበብ በሀገር ግንባታ፣ ለማትና ሰላም አስተዋጾው የጎላ መሆኑን ጠቁመው የዘርፉ ባለሙያዎች በህልውና ዘመቻው በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

“ማናችንም  የግል አመለካከት ሊኖረን  ይችላል፤ በሀገር ጉዳይ ግን ሁላችንም  ከአንድነትና ከመተባበር ውጭ ምርጫ የለንም” ሲሉም ወይዘሮ ሰዓዳ  አመልክተዋል ።

በምክክር መድረኩ ከተሳተፉና ደም ከለገሱ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መካከል አርቲስት ሞአታ ሸኔ “ግንባር ድረስ በመዝመት ጠላትን የሚፋለም መሪ ማግኘታችን ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥሮልናል” ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሞክሮ ከቤተሰብ ደረጃ እስከ የበላይ አመራር ባለው እርከን ሊወርድና ሊጎለብት እንደሚገባ በመግለጽ እርሱም የእርሳቸውን አርአያ ለመከተል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

አርቲስት እልፍነሽ ሰይፉ በበኩሏ “የሀገርን ህልውና ለማስከበር የህይወት መስዋእትነት እየከፈለ ላለው ለመከላከያ ሰራዊት ደም መለገስ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ግንባር ድረስ መዝመት አለብን” ብላለች።

 የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጠላት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከከፈተበት እለት አንስቶ ለህልውና ትግሉ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በፊልምና በሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች መከላከያ ሰራዊቱን እያበረታቱ ስለመሆናቸው በምክክር መድረኩ ተመላክቷል ።