በመቱ ከተማ የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተጀመረ

67

መቱ፤ ህዳር 21/2014 (ኢዜአ) በኢሉባቦር ዞን መቱ ከተማ ከ3ሺህ 500 በላይ ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት የሴፍቲኔት መርሃ ዛሬ ተጀመረ ።
መረሃ ግብር በተጀመረበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የመቱ ከተማ የምግብ ዋስትናና የዜጎች ኑሮ ማሻሻያ የሴፍቲኔት መርሐ-ግብር አስተባባሪ አቶ ዳኛቸው ዘሪሁን እንዳሉት፤ መረሃ ግብሩ  በዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ  ዘንድሮን ጨምሮ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚካሄድ ነው።

ዓላማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የከተማ ማኅበረሰብ አባላት የስራ ዕድሎችን በመፍጠር የኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻል ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም 3ሺህ 549  ሰዎች በቀጥታ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

ተጠቃሚ የሚሆኑት በከተማ ንጽሕና፣ በአረንጓዴና የመሰረተ ልማት ስራዎች፣ የከተማ ግብርናና በሌሎችም ዘርፎች ተሰማርተው በሚያገኙት ገቢ  እንደሆነ አስረድተዋል።

ለስራው ማስፈጸሚያም  ከ7ሚሊዮን 700ሺህ ብር በላይ መመደቡን አቶ ዳኛቸው አስታውቀዋል።

በመረሃ ግብሩ ከሚሳተፉት ውስጥ  60 በመቶ   ሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ በየጊዜው ከሚከፈላቸው ገንዘብ ሃያ በመቶውን ከሚቀጥቡት በተጨማሪ በአምስት ዓመቱ  መጠናቀቂያ ለእያንዳንዳቸው የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው የተመለከተው።

ይህንን ተጠቅመው እራሳቸውን ችለው ኑሯቸውን እንደሚያሻሽሉ ይጠበቃል።

የኢሉባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ካሳሁን በበኩላቸው፤ የመርሀ ግብሩ ዓላማ መሳካት ለሌሎችም ሰዎች የሚጠቅም መሆኑን ጠቅሰው፤ ተሳታፊዎቹ አጋጣሚውን በአግባቡ ሊገለገሉበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዋነኛ ግቡ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል  እንደሆነ ገልጸው፤ ይህንን ዕውን በማድረግ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና መረጋገጥም በመረሃ ግብሩ  ከታቀፉት ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

በመረሃ ግብሩ ሌሎችንም ተጠቃሚ ለማድረግ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።

በተጀመረው መረሃ ግብር ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አቶ ፈድሉ ሸረፈዲን በሰጡት አስተያየት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና በዚህም ከነቤተሰቦቻቸው ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት በአንድ በኩል የሀገርን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጋረጠብንን ፈተና እየተጋፈጠ በሌላ በኩል የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር እንዲህ ዓይነት ዕድልን መፍጠሩ ሕዝባዊነቱን የበለጠ ያጎለዋል ብለዋል።

ባገኙት ዕድልም የከተማቸውን ንጽሕና በመጠበቅና በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በመሰማራት አካባቢያቸው የሚለወጥበትንና እርሳቸውም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስራ ላይ ጠንክረው  እንደሚንቀሳቀሱ ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ በዘለለ ቦጋለ በበኩላቸው፤ ለረዥም ዓመታት በሰው ቤት እንጀራ በመነጋገር ልጆቻቸውን ሲያስተዳድሩ ይቸገሩ እንደነበር  አስታውሰው፤ በመርሃ ግብሩ መታቀፋቸው ኑሯቸውን  ለመሻሻል እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

በሚኖራቸው ቆይታ ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጥበትን ስራ በማከናወንና የቁጠባ ባሕል በማዳበር ለመለወጥ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

ሌላዋ የመረሃ ግብሩ ተሳታፊ ወጣት ሺብሬ ታዬ ፤ ባገኘችው ዕድል በአግባቡ ተጠቅማ ሕይወቷን ለመለወጥ እንደምትንቀሳቀስ ነው የገለጸችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም