የውጭ ጫናዎችን የመከላከል ዲፕሎማሲዊ ጥረቶች ስኬት እያስመዘገቡ ነው

87

ህዳር 21/2014 /ኢዜአ/  በኢትዮጵያ የሚደርሰውን የውጭ ጫና ለመከላከል የሚደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ስኬት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ያልተገባ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እያደረጉ ነው።

በተለይም ሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ወደ ትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እውቅና የመንፈግ አካሄድ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪ የተፈጸሙ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ለማጣራትና የድርጊቱ ፈጻሚ አካላት ላይ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያደርገውንም ጥረት ከቁብ ያለመቁጠር ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የታላቁ ሕዳሴ ግደብን የዓለም የጸጥታ ስጋት አስመስሎ በማቅረብ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በመንግስታቱ ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ እንዲያልቅ የሚያደርጉትን ጥረትም ሌላኛው ጫና መሆኑን ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም የሱዳን መንግሥት በሕገ-ወጥ መልኩ የኢትዮጵያን መሬት መያዙንና ይህም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና የብሔራዊ ጥቅሟን የሚገዳደር የውጭ ጫና መሆኑንም ነው የተናገሩት።

እነዚህን ወቅታዉ ጉዳዮችን ተንተርሶ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉትን ያልተገቡ ጫናዎች ለመከላከልና ለመቋቋም የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ውጤታማ  መሆናቸውን  አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የቀድሞ የአሜሪካና የምዕራብ አገራት ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት ውይይት ሕጋዊ መንግሥትን ለመገልበጥ የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ አይነቱ አካሄድም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ቻርተር አልያም ደግሞ የአገራትን ግንኙነት በሚወስኑ ዓለም አቀፍ ሕጎች ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመገልበጥ በሚያሴሩ የውጭ ዲፕሎማቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ደያስፖራውም በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።     

በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን የውጭ ጫና ለመከላከል የተጀመረው የ "በቃ" ንቅናቄ /No More Movement/ ጉዳዩን አፍሪካዊ ጭምር በማድረግና ጫናውንም በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

በዚህ ንቅናቄ ውስጥ አፍሪካዊ ታዋቂ ሰዎች መቀላቀላቸው ኢትዮጵያ የያዘቸውን አጀንዳ የአፍሪካዊ ጉዳይ እንዲሆንና ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት እንዲያገኝ ያስቸለዋልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም