ለሽብር ተግባር የሚውል ህገ-ወጥ መታወቂያ እያዘጋጀ ሲያድል የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

102

ድሬዳዋ፣ ህዳር 21/2014 (ኢዜአ) ለሽብር ተግባር የሚያገለግል ህገ-ወጥ መታወቂያ በማዘጋጀት ሲያድል የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ ኮሚቴ አስታወቀ።

የእዙ አባል የሆነው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የጎሮ ፖሊስ ጣቢያ አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ያሲን አህመድ ለኢዜአ  እንደገለጹት ግለሰቡ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ባለፈው ቅዳሜ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ  በከተማው ሣቢያን ቀበሌ ቶኒ እርሻ በተባለ አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ለሽብር ተግባር የሚውሉ ሀሰተኛ መታወቂያዎችና ሰነዶች በማዘጋጀት ላይ እንዳለ እጅ ከፍንጅ መያዙን ተናግረዋል።

ፖሊስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ መሰረት ባደረገው ፍተሻ ከተያዙ መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው  የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ሀሰተኛ መታወቂያ ካርዶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ከመታወቂያ ካርዶቹም መካከል ዝግጅታቸው የተጠናቀቀ እንዲሁም የግለሰቦች ፎቶና ማህተም ያላረፈባቸው በዝግጅት ሂደት ላይ ያሉ  እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም መታወቂያ የሚዘጋጅላቸው የበርካታ ግለሰቦች ፎቶግራፎች፣ ማህተሞችና ሌሎች ህገወጥ ሰነዶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።

የሽብር ተግባራት ተልዕኮ ከሚፈጸሙባቸው መካከል ህገ-ወጥ ሰነዶችና ማንነት መገለጫ የመታወቂያ ካርድ ተጠቃሽ መሆናቸውን  የገለጹት ኢንስፔክተር ያሲን ፖሊስ ተጠርጣሪ ግለሰቡን  በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በሣቢያ ጎሮና አካባቢው  በተደረገ ቁጥጥርና የቤት ለቤት ፍተሻ በርካታ ቦንቦች፣ ሹጉጦችና ሌሎች ተቀጣጣይ መሣሪያዎች መገኘታቸውን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ያሲን መሳሪያ የተገኘባቸውን ጨምሮ ከአሸባሪዎቹ ከህወሃትና ከሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ ኮሚቴ አባል የሆነው የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነትና የለውጥ ሥራዎች ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ ሽብርተኞች እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው የሽብር ተግባራት ለመፈጸም እንዲችሉ ሲዘጋጅ የነበሩ የህገ-ወጥ የመታወቂያ ካርድ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት ፖሊስና ነዋሪው ሌት ተቀን ተቀናጅተው በመስራታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ የወንጀሉን ሰንሰለት መነሻና መዳረሻ ለማግኘት ጥብቅ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል ።

እንደ ኮማንደር ገመቹ ካቻ ገለጻ የድሬዳዋ ፖሊስና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው የአካባቢን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ እንዲሁም የሽብርተኞቹን ህወሃትና ሸኔ ሴራና ተላላኪዎችን ለማጋለጥ እያከናወኑ ያሉት ተግባራት ፍሬ እያፈሩ ናቸው፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ ኮሚቴ  ከሁለት ቀን በፊት በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 14 ማዳበሪያ ከረጢት አደገኛ ዕፅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።