የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫናና ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ተፅእኖ መጠናከር አለበት

249

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2014(ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና እና ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ተፅእኖ መጠናከር አለበት ሲሉ የአፍሪካ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ተንታኙ ሎውረንስ ፍሪማን ተናገሩ።

ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱት ያልተገባ ጫና እና ጣልቃገብነት መላው አፍሪካን የሚመለከት በመሆኑ ሁሉም በጋራ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

ሎውረንስ ፍሪማን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በቀድሞ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና በሽብርተኛው ሕወሃት ሰዎች የተደረገው ምስጢራዊ የዙም ውይይት በህጋዊ መንገድ ሚሊየኖች የመረጡትን መንግስት ለማስወገድ መሆኑን ገልጸዋል።

የቀድሞ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ተሳትፎ የአሜሪካን መንግስት አቋም ነው ተብሎ ባይወሰድም በባለስልጣናቱ ግን መወገዝ ነበረበት የሚል እምነት አላቸው ሎውረንስ።

የጆ ባይደን አስተዳደር ሚሊየኖች ተሳትፈውበት በህጋዊ ምርጫ ለተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዕውቅና አለመስጠቱም አሜሪካ ዴሞክራሲን በተግባር እንደማትደግፍ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣትና ህዝቧን ተጠቃሚ ለማድረግ እየገነባችው ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአሜሪካ መንግስት አለመደገፉ አስገርሞኛል ነው ያሉት።

የአሜሪካ መንግስትንና ምዕራባናዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃገብት ለመቋቋምም ኢትዮጵያዊያን ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ በጋራ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

በአሜሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የምእራባዊያኑን ድርጊት ለመቃወም እያደረጉት ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ አድንቀው አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም የአሜሪካ ዜግነታቸውን ተጠቅመው በኢትዮጵያ እና ምስራቅ አፍሪካን ለማተራመስ የምታራምደውን ፖሊሲ በምርጫ ካርዳቸው ለማስለወጥ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የዘውገኝነት ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ብሎም ለመላው አፍሪካ ስጋት ነው ያሉት ፍሪማን፤ ይህ ጉዳይ ትልቅ ጥንቃቄ የሚሻ እንደሆነ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣ ጥቃት የመላው አፍሪካ ነው፤ የተጋረጠባት የህልውና አደጋም ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የነበራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚገታ ነው ብለዋል።

በአድዋ ጦርነት በባዶ እግራቸው ቅኝ ገዥዎችን ድል በማድረግ ኢትዮጵያን ያለ ቅኝ ግዛት ያዘለቁ ህዝቦቿ ታሪክ የማይዘነጋቸው መሆኑን አስታውሰው የአሁኑም ትውልድ ለክብሯ በጋራ መቆም አለበት ብለዋል።

በ1928 የፋሺስት ኢጣሊያ በወረራት ጊዜ አፍሪካዊ አሜሪካዊያን እና የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች ቪዛ ተከልክለው ባይሳካላቸውም ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት እንቅስቃሴ ስለማድረጋቸውም አስታውሰዋል።

የአፍሪካዊያንን የጋራ ታሪክ የያዘች የነጻነት ትምህርት የሆነችው ኢትዮጵያ የሚፈጠርባት የምዕራባዊያን ጫና መላው አፍሪካን የሚጎዳ ነው ብለዋል።

አሁንም ኢትዮጵያ ያጋጠማት የሕልውና አደጋ የአፍሪካዊያን የጋራ ትግል በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚሰለፉ አንጠራጠርም ብለዋል።