አገር የማፍረስ ሙከራው በኢትዮጵያ ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ አፍሪካውያን የ "#በቃ" ዘመቻን በሰፋት መቀላቀል አለባቸው

86

 አዲስ አበባ ህዳር 21/2014 /ኢዜአ/  "በሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ስም የሚደረገው አገር የማፍረስ ሙከራ በኢትዮጵያ ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ አፍሪካውያን የ "#በቃ" ዘመቻን በሰፋት መቀላቀል አለባቸው" ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ጥሪ አቀረበ፡፡
አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት በማይመጥን መልኩ ጫና ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ነው ያነሳው፡፡

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ በኢትዮጵያ ላይ አገር ማፍረስን ዓላማ ያደረገ  የውክልና ጦርነት እንደተከፈተባት ተናግሯል፡፡

"በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን አገራችንን ለማዳን ያለ ልዩነት ከጫፍ ጫፍ ተነስተናል ብሏል፡፡

አንዳንድ የምእራባውያን አገራት ከዚህ ቀደም በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ስም በርካታ አገራትን ማፍረሳቸውን ገልጾ፤ በዚህ ረገድ አፍሪካዊቷን ሊቢያ በአብነት አንስቷል፡፡

የጥቂት የምእራባውያን ኩባንያዎችን ገቢ ለማካበት ሲባል አፍሪካ ሰላሟን ማጣት የለባትም  ነው ያለው፡፡

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን "#በቃ" በሚል ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ከጎናችን መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠውልናል ሲልም ነው የተናገረው፡፡

በዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ስም የሚደረገው አገር የማፍረስ ሙከራ በኢትዮጵያ ብቻ የሚያቆም አለመሆኑን የሚገልጸው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ከዚህ አኳያ መላው አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አዲስ መልክ ይዞ እየመጣ ያለውን ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ሊታገሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረው "# በቃ" ዘመቻ ጦርነትን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ለመበዝበዝ የሚደረግ የትኛውንም አይነት ሴራ የሚቃወም መሆኑንም አብራርቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት አፍሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ መመልከት እንዳለባቸው በመግለጽ፡

መላው አፍሪካውያን ብሎም የጥቁር ህዝቦች  “ኢትዮጵያ ምን በማድረጓ ነው ይህ ሁሉ ጫና ያረፋባት?” ሲሉ መጠየቅ እንደሚገባቸውም ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት በማይመጥን መልኩ ጫና ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ዜጎች መንግስቶቻቸውን "ለምን ኢትዮጵያ ላይ?" በማለት መጠየቅ እንዳለባቸውም ነው ያነሳው፡፡  

የትግራይ ወገኖቻችን ለክፋ እንግልትና ስቃይ የዳረጓቸውን የአሸባሪው ህወሃት መሪዎችንና የውጭ ግብረ አበሮቻቸውን "# ብቃ" በማለት ሊታገሏቸው እንደሚገባም አትሌቱ ተናግሯል፡፡

የአሸባሪው ህወሃት መሪዎች በኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች እየተጋለቡ የትግራይ ህዝብን ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹና ከመላው የአፍሪካ ህዝብ ጋር ለማጋጨት እየሰሩ መሆኑንም ነው ያብራራው፡፡

ኢትዮጵያ አሳድጋና አስተምራ ለትልቅ ደራጃ ያደረሰቻቸው ኢትዮጵያውያን በዚህን ወቅት ከአገራቸው ጎን መቆም አለባቸው ነው ያለው፡፡

"ግለሰቦች ሰውን ሊበድሉ ይችላሉ፤ አገር ግን ዜጎቿን በድላ አታውቅም" የሚለው አትሌቱ፤ ከዚህ አኳያ ግለሰቦች በፈጸሙት በደል አገር ልትተው አይገባም ብሏል፡፡

በመሆኑም በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው በመቆም የኢትዮጵያ የድል ታሪክ አካል መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡

አትሌት ሻለቃ ኃይለ ገብረስላሴ ለኢትዮጵያ ህልውና እና ሉዓላዊነት በግንባር ከመሰለፍ ጀምሮ የሚጠበቅብትን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

አትሌቱ ከዚህ ቀደም በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም