ትዊተር የተቃውሞ ድምጾችን እያፈነ መሆኑ ተገለጸ

357

ህዳር 21/2014 /ኢዜአ/  ሰዎች በነጻነት ሃሳባቸውን ይገልጹባቸዋል ከሚባሉ የማህበራዊ ድረ-ገጽ አማራጮች መካከል አንዱ የሆነው ትዊተር የተቃውሞ ድምጾችን እያፈነ መሆኑን የስፑትኒክ ዘገባ አመለከተ።

በአሜሪካ የተመራው የምእራባውያን ጫና በአፍሪካ ሃገራት ላይ እያየለ በመምጣቱ የበቃ #NoMore ንቅናቄ በስፋት እየተንጸባረቀ ባለበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን የተቃውሞ አስተያየቶችና ሃሳቦች እየተመረጡ ለሌሎች እንዳይታዩ በመደረግ ላይ ናቸው።

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሃሰትና በተፈበረኩ ዜናዎች ሰላም ሊያጣ እንደማይገባና ኢትዮጵያና ኤርትራን የማጥቆር ዘመቻው እንዲቆም ሲሞግት የነበረው የሆርን ኦፍ አፍሪካ ሃብ የትዊተር መጠቀሚያ ላልተወሰነ ጊዜ የተዘጋ ሲሆን መጠቀሚያው ወደ 19 ሺህ የሚጠጋ ተከታይ እንደነበረውም ዘገባው ገልጿል።

ከ30 በላይ በሚሆኑ ታላላቅ የአለም ከተሞች በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ያንጸባረቋቸው መልእክቶች ተለቅመው ለእይታ እንዳይበቁ መደረጋቸውን ያስነበበው ስፑትኒክ ትዊተር ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን አሞግሰዋል ያላቸውን ጽሁፎችን ከገጾቹ ሲያወርድ መሰንበቱን አስነብቧል።

የኒው አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆነው ሳይመን ተስፋማርያም እጃችሁን ከኢትዮጵያና ከኤርትራ አንሱ በማለት በሚያራምዳቸው ሃሳቦች ምክንያት የትዊተር መጠቀሚያው ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንደተዘጋበት ገልጾ የበቃ #NoMore ንቅናቄ አለም አቀፍ አጀንዳ መሆኑን ተከትሎ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ፖለቲካዊ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ማሳያ ነው ብሏል።

ከምስራቅ አፍሪካዎቹ ኢትዮጵያና ኤርትራ በመሻገር ወደ ምእራብ አፍሪካዎቹ ኒጀርና ቡርኪናፋሶ በመዛመት የፈረንሳይ ወታደሮች እንዲወጡ ተቃውሞዎች መነሳታቸው የንቅናቄውን ውጤታማነት ያሳያል ያለው ሳይመን ትዊተር እያደረገ ያለው ድምጾችን የማፈን እንቅስቃሴ ኢምፔሪያሊዝምን የማስቀጠል ፍላጎት ማሳያ ነው ብሎታል።

የትዊተር ኩባንያ በርካታ የላቲን አሜሪካ ፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎችን መጠቀሚያዎች ሲቆልፍ እንደነበር የኩባ ፕሬዝዳንት ሚግዌል ዳያዝን ለአብነት ያነሳው ዘገባው ኢትዮጵያ ሽብርተኛ ብላ ከፈረጀችው የህወሃት ቡድን ጋር ትስስር ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ያለከልካይ ሃሳባቸውን እያስተላለፉ መሆኑንም ይፋ አድርጓል።