የመተማ ወጣቶች የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት እንደሚያስጠብቁ አስታወቁ

106

መተማ፣ ህዳር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት በማስጠበቅ የአባቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ እንደሚደግሙ በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ወጣቶች አስታወቁ።

ወጣቶቹ በመተማ ወረዳ ኮኪት ከተማ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄደዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ወጣት አህመድ ለጋስ እንዳለው፤ አሸባሪው ህወሓት የደቀነውን ወቅታዊ የህልውና አደጋ በመቀልበስ ኢትዮጵያ አሁንም የማይደፈሩ የጀግኖች እናት መሆኗን ማስመስከር ይገባል።

"በውስጥ ባንዳና በምዕራባዊያን ጫና ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚፈቅድ ስነ ልቦና እና ማንነት የለንም" ብሏል።

"ኢትዮጵያ ጠላት እንዳሰበው አትሆንም ያለው" ወጣቱ፤ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር ወደ ግንባር በመዝመት የሚጠበቅበትን ለመወጣት መዘጋጀቱንም ተናግሯል።

ወጣት ይበልጣል ወንድም በበኩሉ "የሽብር ቡድኑ ብቻ ሳይሆን ክፉ የሚመኙላት ሁሉ በሩቅ የሚፈራትና የሚያከብራት ሀገር እንድትኖረኝ የበኩሌን እወጣለሁ" ሲል ተናግሯል።

ኢትዮጵያዊያን ተባብረው እያካሄዱት ባለው የህልውና ዘመቻ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል  የራሱን አሻራ ለማኖር ቁርጠኝነቱን ገልጿል።

"ሁሉም ዕድሜውና የጤና ሁኔታው የሚፈቅድለት ወጣት መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል የሀገር ፍቅሩን በተግባር መግለጽ ይኖርበታል" ብሏል።

''ተላላኪና አሻንጉሊት መንግስት እንደማይኖረን ከመሪያችን አረጋግጠናል፤ እኛም ወደግንባር በመዝመት አጋርነታችን እናሳያለን'' ያለው ደግሞ ሌላኛው ወጣት ታረቀኝ ጌታሁን ነው።

የሽብር ቡድኑን ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓለማ ለማምከን ህዝቡ በደጀንነት የጀመረው ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቋል።

ኢትዮጵያ ለየትኛውም ጠላት የማትመችና የአፍሪካ ኩራት ሆና እንድትቀጥል ከሰራዊቱ ጎን እንደሚቆም ገልጿል።

በብልጽግና ፓርቲ የወረዳው  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሩ ሙሉጌታ በበኩላቸው የአሁኑ ትውልድ የታሪክ አደራ ያለበት በመሆኑ አደራውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የመከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ኃይልን በመቀላቀል የሀገርን ህልውና ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝቧዋል።

የሽብር ቡድኑ ጦርነት የከፈተው ስልጣን ለመያዝ ሳይሆን ሀገር ለማፍረስ ነው፤ ያሉት ደግሞ በዞኑ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) ሰብሳቢ አቶ አግባው ሰጠኝ ናቸው።

የሽብር ቡድኑ ለኢትዮጵያ የማይበጅ ስብስብ በመሆኑ እኩይ ዓላማውን ከእነ አስተሳሰቡ ጭምር መቅበር የሀገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት በመሆኑ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

የሕልውና ዘመቻውን በድል ማጠናቀቅ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በተለይ ወጣቶች በአሸናፊነት ወኔ ቀደምት አባቶችን  ታሪክ እንዲደግሙ መክረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም