የገንዘብ ኖቶች ለማባዛት በዝግጅት ላይ የነበሩ ሁለት የዉጭ ሀገር ዜጎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

98

ህዳር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትን የገንዘብ ኖቶች ለማባዛት በዝግጅት ላይ የነበሩ የካሜሮን እና የኮትዲቭዋር ዜግነት ያላቸው ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ግለሰቦቹ በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አማዶ የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ እና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አዲስ ብራይት የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ የገንዘብ ኖቶችን  በማዘጋጀት ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር ዉለዋል፡፡

የግለሰቦቹን ህገወጥ እንቅስቃሴ ሲከታተል የነበረዉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተጠርጣሪዎቹን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥቆማ በመስጠት በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ አድርጓል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሲዉሉ 107 ሺህ 330 ትክክለኛ የኢትዮጵያ ብር፣ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች፣ ባለ 200 በርካታ ፎርጅድ የኢትዮጵያ ብሮች፣ ዱቄት መሳይ ኬሚካል፣ ፈሳሽ ኬሚካሎች፣ የወረቀት መቁረጫ፣ በርካታ ቾክ፣ በርካታ ወረቀት፣ 9 ሞባይል ስልኮች እና ሌሎች ቁሳቁሶች መያዛቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም