የሃይማኖት ተቋማት ለኢትዮጵያ ክብርና ለህዝቦች አንድነት የላቀ ሚና አላቸው

156

ህዳር 20/2014 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት ለኢትዮጵያ ክብርና ለህዝቦች አንድነት የላቀ ሚና አላቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ስለ ሀገራችን ሰላምና አንድነት በመተባበር እንስራ በሚል ሃሳብ በዛሬው እለት የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ማህበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወን በማሰብ ውይይቱ መዘጋጀቱም ታውቋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የኃይማኖት ተቋማት ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር እንድታልፍ ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት ሁላችንም በጋራ ልንሰራ ይገባል ያሉት ከንቲባዋ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ ደግሞ ለዚህ ላቅ ያለ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የበለፀገችና ሰላሟ የተጠበቀች አገር ለመገንባት በኢትዮጵያ ላይ የተነሱትን የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች መክቶ ማሸነፍ ግድ ይለናል ብለዋል።

የኃይማኖት መሪዎች ለተከታዮቻቸው ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን በማስተማር ለአገራቸው ህልውና በጋራ እንዲቆሙ የማስተባበር ድርሻቸው የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲሁም ለህዝቦች አንድነት የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል ከንቲባዋ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የውጭ ግኑኝነትና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፤ ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ የኖረች ታላቅ አገር ነች አሁንም ትቀጥላለች ብለዋል።

ቤተ-እምነቶች ስለ ሰላም፣ አንድነት አብዝተው ማስተማር እና መጸለይ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ምዕመኑም የሚሰጠውን ትምህርት ከመስማት ባለፈ መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ ይልማ ጌታሁን፤ የእምነት ተቋማት በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም የአገር አንድነት እንዲጠበቅ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

የእምነት ተቋማት ከሚሰጧቸው መንፈሳዊ ትምህርት ባሻገር ሰዎች የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ መሥራት ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።